የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ኮቪድ 19 እንደያዛቸው ተገለጠ፡፡ ኋይት ሐውስ ይህን ያስታወቀው ትላንት ፕሬዚደንቱ ኔቫዳ ክፍለ ግዛት ላስ ቬጋስ ከተማ ውስጥ ለትውልደ ላቲን አሜሪካ ማኅበረሰብ የድጋፍ ተማጽኖ ለማቅረብ የነበራቸው እቅድ በድንገት ከተሰረዘ በኋላ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ባይደን ወደዴላዌር ለመጓዝ ኤር ፎርስ ዋን ፕሬዚደንታዊ አውሮፕላን ላይ ሊሳፈሩ ሲሉ ለነበሩት ጋዜጠኞች “ደህና ነኝ” ብለዋቸዋል፡፡
የሰማኒያ አንድ ዓመቱ ባይደን ኮቪድ እንደያዛቸው የታወቀው ትላንት ላስ ቬጋስ ላይ ከተገኙበት የመጀመሪያው የምርጫ ዘመቻቸው ተከትሎ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የኋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ ካሪን ዣን ፒየር ባወጡት መግለጫ የኮቪድ 19 ክትባት ከነማጠናከሪያው የተከተቡት ባይደን ያላቸው “መለስተኛ የሆነ የኮቪድ ህመም ምልክት” ነው ብለዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ ዴላዌር ሮሆቦት በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ራሳቸውን ለይተው ተቀምጠው ሙሉ ሥራቸውን እያከናወኑ እንደሚቀመጡም ቃል አቀባያቸው አመልክተዋል፡፡
ከተል ብለው የፕሬዚደንቱ ሐኪም ባወጡት መልዕክት ተከታታይ የአፍንጫ ፈሳሽ ሳል እና አጠቃላይ የድካም ስሜት የሚታይባቸው ፕሬዚደንቱ የአተነፋፈስ ሁኔታቸው የሰውነት ሙቀታቸው እና የደም ውስጥ ኦክሲጂን መጠናቸው በሙሉ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ፓክስሎቪድ የተባለው መድሃኒት እንደተጀመረላቸውም ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ባይደን በድጋሚ ለመመረጥ ፉክክር እንዲወጡ ትላንት በዲሞክራቲክ ፓርቲያቸው አባል ተጠይቀዋል፡፡
ዲሞክራቱ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል አዳም ሺፍ ባወጡት መግለጫ “ዶናልድ ትረምፕ ቢያሸንፉ ራሱን የዲሞክራሲያችንን መሠረት የሚያናጋ አደጋ ይሆናል” በማለት ያስጠነቀቁ ሲሆን ባይደን ማሸነፍ የመቻላቸው ዕድል በእጅጉ አሳስቦኛል” ብለዋል፡፡
ኮንግሬስማን አዳም ሺፍ አክለው “የምርጡኝ ዘመቻቸውን ማቋረጥ ወይም አለማቋረጥ የፕሬዚደንቱ ውሳኔ ብቻ ቢሆንም በእኔ እምነት ግን አሁን ለሌላ ተወዳዳሪ ለቅቀው መውጣት አለባቸው” ብለዋል፡፡ “ያን ካደረጉ” አሉ ሺፍ በመጪው ምርጫ ዶናልድ ትረምፕን እንድናሸንፍ ዕድል የሰጡ መሪ ሆነው ታሪካቸው ይመዘገብላቸዋል”
መድረክ / ፎረም