በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሽብር ጥቃት ሊያደርሱ በማሴር የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች በቤልጅም ተያዙ


የቤልጅም አቃብያን ህግ፣ የብራስልስ ከተማ ፖሊሶች በዚህ የዓውዳመት ወቅት ጥቃት ሊያደርሱ በማሴር የተጠረጠሩ ሰዎችን እንደተያዙ ገልጸዋል።

ዛሬ ቤልጂም ውስጥ በዋና ከተማዋ ብራስልስ በዚህ የዓውዳመት ወቅት የሽብር ጥቃት ሊያደርሱ በማሴር የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች በፖሊሶች መያዛቸውን አቃብያን ህግ ተናገሩ።

በመጪው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ ብራሰልስ ውስጥ ያሉ በርካታ ታዋቂ ስፍራዎች ላይ ከባድ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል የሚጠቁሙ ማስረጃዎች መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

የጥቃት ዒላማ ይሆናሉ ተብሎ ያሰጉትን ቦታዎች የአቃቢያን ህጉ ጽህፈት በዝርዝር አልገለጸም። ብራስልስ የቤልጂየም ዋና ከተማ ከመሆንዋም በተጨመሪ የአውሮፓ ህብረት የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት እና የበርካታ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት መስሪያ ቤቶችም መቀመጫ መሆንዋ የሚታወቅ ነው።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከትናንት በስቲያ ዕሁድና ትናንት ሰኞ የተያዙት ብረሰልስ እና ሊዥ ከተማ አጠገብ በተደረገ ፍተሻ ወታደራዊ መሰል መለዮ ልብሶችና የእስልምና መንግሥት ቡድን የፕሮፓጋንዳ ወረቀትና ቁሳቁስ ከተገኙ በኋላ ነው። ባለስልጣናቱ እንዳሉት ፈንጂ ወይም ሌላ መሳሪያ ግን አልተገኘም።

መጀመሪያ ላይ የተያዙት ስድስት ሰዎች እንደነበሩና አራቱ እንደተለቀቁ ታውቋል። ከታሰሩት አንዱ የሽብር ቡድን በመምራት እና ሌሎችን ለሽብር ተግባር በመመልመል ወንጀል ተከሷል።

XS
SM
MD
LG