በባንግላዴሽ በትላንትናው ዕለት አዲስ የተሾሙት መሪ ዛሬ ሐሙስ ከፓሪስ ሃገራቸው ገብተዋል።
ጊዜያዊ መንግስቱን እንዲመሩ በሃገሪቱ ኤታማዦር ሹም ሥልጣን የተሰጣቸው የ84 ዓመቱ የኖቤል ሰላም ሽልማት አሸናፊው ሙሃማድ ዩኑስ፣ ሃገራቸው ሲገቡ በኤታማዦር ሹሙ ጀኔራል ዌከር ዛማን አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ዛሬ ምሽት ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ ይጠበቃል።
“ዛሬ ለእኛ ታላቅ ቀን ነው። ባንግላዴሽ አዲስ የድል ቀን ፈተረች። ባንግላዴሽ ሁለተኛ የነፃነት ቀን አገኘች።” ሲሉ በአየር ማረፊያው እንደደረሱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ዩኑስ በሠራዊት አዛዡ የተሾሙት የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሃሲና በደረሰባቸው የሕዝብ ተቃውሞ ሃገር ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
ተቃውሞው የተነሳው መንግስት ሥራን በኮታ ለመሥጠት በመወሰኑ እንዲሁም ሼክ ሃሲና ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩ፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚጠየቁና ምርጫ ያጭበረበሩ ናቸው በሚል ነበር።
በተቃውሞው 300 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በሁከቱ ተሳታፊ የሆኑ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የኤታማዦር ሹሙ ጀኔራል ዌከር ትላንት አስታውቀዋል።
ፕሬዝደንት ሞሃመድ ሻሁቡዲን ትላንት ማክሰኞ ፓርላማውን በትነዋል። ይህም ዩኑስ ጊዚያዊ መንግስቱን እንዲመሩ ጥርጊያ መንገድ ይከፍትላቸዋል ተብሏል።
በበንግላዴሽ አዲስ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ ገና አልታወቀም።
መድረክ / ፎረም