ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 26/2014 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው 33 የፓርቲው አባላት የካቲት 23 በተከበረው 126ኛው የአድዋ እና በየካቲት 26ቱ የካራማራ ድል በዓላት ላይ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሞክረዋል በሚል እንደጠረጠራቸው ለፍርድ ቤት ማሳወቁን የታሳሪዎቹ ጠበቃ ገልጸዋል፡፡ የካራማራ የድል በዓል ለማክበር የካቲት 26/2014 ዓ.ም በድላችን ሀውልት (ኢትዮ- ኩባ) አደባባይ ከተገኙ 33 አባሎቼ በዕለቱ በግፍ ታስረውብኛል ያለው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ እስረኞቹ ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አስታውቋል፡፡
ከነዚህም 31ዱ እስረኞች በቀረቡበት ፍርድ ቤት የተገኙት የታሳሪዎቹ ጠበቃ ቤተማሪያም አለማየሁ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንፈቀደለት ተናግረዋል።