በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሠራ ፓርቲው አስታወቀ


የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሠራ ፓርቲው አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:14 0:00

የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሠራ ፓርቲው አስታወቀ

የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ፣ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋራ በመተማመንና በመተባበር እንደሚሠራ፣ የዐማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ::

በክልሉ ርእሰ መዲና ባሕር ዳር ከተማ፣ ላለፉት ሦስት ቀናት ሲካሔድ የቆየው የዐማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ኮንፈረንስ ሲጠናቅቅ፣ ፓርቲው በአወጣው የአቋም መግለጫ፣ የዐማራ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው፣ የኢትዮጵያዊነት ማሕቀፍን በአስቀደመ መልኩ ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር እንደኾነ አስታውቋል፡፡ ለዚኽም የፓርቲው መሪዎች፣ አስፈላጊውን መሥዋዕት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን አመልክቷል፡

የዐማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ(አዴኃን) እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን በበኩላቸው፣ ውለው ያደሩ ያሏቸው የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት፣ የዐማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ፣ ከመግለጫ ባለፈ መሬት ላይ የወረደ ሥራ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመር አለበት፤ ብለዋል፡፡

የዐማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ ለሦስት ቀናት ያህል ሲያካሒዱት የሰነበቱት ውይይት ተጠናቋል፡፡ የውይይቱ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ፓርቲው በአወጣው የአቋም መግለጫ፣ የዐማራ ሕዝብ ፖለቲካዊ ችግር፣ ሥር የሰደደ እና የተወሳሰበ እንዲኾን የተደረገው፣ “በፀረ ኢትዮጵያ እና ፀረ ዐማራ አቋም ህልውናቸውን የመሠረቱ” ሲል በገለጻቸው ቡድኖች የተሳሳተ የታሪክ አረዳድ እንደኾነ አስገንዝቧል፡፡

በውይይቱ መክፈቻ ላይ፣ የዐማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፣ “ያደሩ” ብለው የጠቀሷቸው የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች፣ “የወሰንና የማንነት፣ የሕገ መንግሥት መሻሻል፣ የዜጎች መብት መከበር፣ የጨቋኝ እና ተጨቋኝ ትርክቶች ይስተካከል” የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚኽ የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚፈቱትም፣ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው፤ ማለታቸው ይታወሳል።

ፓርቲው በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ በያዘው የጋራ አቋም፣ ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ፣ ውስጣዊ አንድነትን ከማጠናከር ባለፈ፣ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋራ በመተማመንና በመተባበር እንደሚሠራ ገልጿል፡፡

የዐማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ(አዴኃን) ሊቀ መንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ፣ “ያደሩ የዋሉ” ሲሉ የገለጧቸው የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋራ በማበር እንደኾነ አሥምረውበታል፡፡ ለዚኽም፣ የዐማራ ብልጽግና ፓርቲ አሁን የያዘው አቋም ትክክለኛ ነው፤ ብለዋል፡፡

በውይይቱ፣ ፈተናዎችንና የመውጫ ስልቶችን መለየቱን የገለጸው፣ የዐማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ፣ የጋራ ቅቡልነት ያገኘ መንግሥትን ለመገንባት የሚያስችል የኅብረ ብሔራዊ ሒደት አማራጭን አስቀድመናል፤ ብሏል፡፡

የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች፣ ፍትሐዊ እና ተገቢነቱ የማያጠራጥር ነው፤ ያለው ፓርቲው፣ ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ፣ ሁሉንም ዐይነት መሥዋዕት ለመክፈል ዝግጁ እንደኾነ፣ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር፣ ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም አሐዱ፣ ፓርቲው ችግሮችን ከመለየት እና ከመተንተን ባለፈ፣ መሬት ላይ የወረደ ሥራ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመር አለበት፤ ብለዋል፡፡

በዚኹ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር የኾኑት ረዳት ፕሮፌሰር ያያው ገነት ደግሞ፣ የሕዝቡ ጥያቄዎች፣ መሠረታዊ ሀገር አቀፍ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው በመኾኑ፣ በቅድሚያ የፓርቲ ሥርዐቱ ቅድሚያ መስተካከል እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡

“ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ቃል፣ ለሦስት ቀናት የተካሔደው፣ የዐማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ውይይት ቀጣይ ምዕራፎች እንደሚኖሩት ተጠቁሟል፡፡

XS
SM
MD
LG