በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በባሕር ዳር በእግር ኳስ ደጋፊዎች ላይ በተወረወረ ቦምብ ጉዳት ደረሰ


በባሕር ዳር በእግር ኳስ ደጋፊዎች ላይ በተወረወረ ቦምብ ጉዳት ደረሰ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:27 0:00

በባሕር ዳር በእግር ኳስ ደጋፊዎች ላይ በተወረወረ ቦምብ ጉዳት ደረሰ

ከባሕር ዳር ወደ ሐዋሳ ለመጓዝ፣ አውቶብስ በመሳፈር ላይ በነበሩ የባሕር ዳር ከተማ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ላይ፣ በተወረወረ የእጅ ቦምብ፣ በ23 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን፣ የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ገለጹ። በጥቃቱ እስከ አሁን ሓላፊነት የወሰደ አካል የለም።

በባሕር ዳር ከተማ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ላይ የቦምብ ጥቃቱ የተፈጸመው፣ ትላንት ከሌሊቱ 10፡45 ላይ እንደነበር፣ የከተማው ከንቲባ እና የባሕር ዳር ከተማ የእግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት ዶር. ድረስ ሣህሉ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

በአንገቱ እና በእግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት፣ በፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በሕክምና ሲረዳ ያገኘነው እና ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ የክለቡ ደጋፊ፤ ወደ አውቶብሱ ሊገቡ ሲሉ፣ ከኋላቸው እየሮጠ የመጣ ሰው መመልከቱንና ወዲያውኑ ፍንዳታው መከሠቱን ተናግሯል።

የባሕር ዳር ከተማ የእግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይገርማል፣ ፍንዳታው ከእርሱ በቅርብ ርቀት ላይ የተከሠተ በመኾኑ፣ በምንና እንዴት እንደተከሠተ አለማየቱን ይናገራል። ነገር ግን የቆሰሉትን ወዲያውኑ ማንሣቱን ይገልጻል።

የከተማዋ ከንቲባ ዶር. ድረስ በበኩላቸው፣ የባሕር ዳር ከተማን ሰላም የሚነሳ ጥቃት ሲፈጸም የመጀመሪያ እንዳልኾነ በማውሳት ድርጊቱን ኮንነዋል።

ከንቲባው አክለውም፣ “ከተማውን በማሸብር መንግሥትን የጠመዘዙ የሚመስላቸው” ያሏቸውንና ማንነታቸውን ያልጠቀሷቸውን አካላት ለጥቃቱ ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

ከዚኽ በኋላ መንግሥት፣ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር ያመለከቱት ከንቲባው፣ ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በጥቃቱ እስከ አሁን ሓላፊነት የወሰደ ኃይል የለም፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው የባሕር ዳር ከተማ፣ ነገ ከሊጉ መሪ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋራ በሐዋሳ ይጫወታል። ጨዋታው በተያዘለት መርሐ ግብር፣ ነገ ምሽት 12 ሰዓት ላይ፣ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም እንደሚካሔድ፣ የፕርሚየር ሊጉ አክስዮን ማኅበር፣ ለአሜሪካ ድምፅ አረጋግጧል፡፡

XS
SM
MD
LG