በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውራምባ ታይምስ ጋዜጠኛ በአዲስ አበባ ታሰረ


የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታየ በኢትዮጵያ መንግስት ሃይሎች መታሰሩን የጋዜጠኛው ቤተሰቦችና የስራ ባልደረቦች አስታወቁ።

ውብሸት ታየ እሁድለት በጸጥታ ሃይሎች ከመኖሪያ ቤቱ ከተወሰደ ወዲህ ወዳጅ ዘመድ እንዳይጠይቀው መደረጉን የዝግጅት ክፍላችን ተረድቷል።

ጋዜጠኛው የታሰረው 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ መሆኑን በመረዳት ልትጠይቀው የሄደችው ባለቤቱ እንድታየው አልተፈቀደላትም። ስንቅና ልብስ ለፖሊስ ባልደረቦች አስረክባ መመለሷን ወይዘሮ ብርሃን ተስፋየ ገልጻለች።

ውብሸት ታየ የተመሰረተበትን ክስ ለማጣራት የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ወደተለያዩ የፖሊስ ባለስልጣናት ባደረገው ማጣራት፤ “እስራቱ ከጋዜጠኝነት ስራ ጋር የተገናኘ አይደለም” የሚል መልስ አግኝቷል።

የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ዳዊት ከበደ ውብሸት በታሰረበት ወቅት ጋዜጦችና ሌሎች የስራ መሳሪያዎችን በፍተሻ ፖሊስ መውሰዱ፤ በሌላ ወንጀል ከተፈለገ አስፈላጊ አልነበረም ብሏል።

የውብሸት ታየ ባለቤት ወይዘሮ ብርሃን የፖሊስ ባልደረቦች በቤታቸው ተገኝተው፤ የፍርድ ቤት የእስርና የፍተሻ ፈቃድ ማሳየታቸውን ትናገራለች።

“በሽብር ወንጀል ስለተጠረጠረ ነው የተባልንው” ስትል ወይዘሮ ብርሃን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጻለች።

የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ በስራ ባልደረባቸው ላይ የተመሰረተውን ክስ በይፋ እንዲያውቁትና፤ ከመናገር ነጻነት ገደብ ጋር የተገናኘ አለመሆኑ በመረጃ እንዲረጋገጥ ጠይቀዋል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG