በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአወዛጋቢዋ አውራ ጎዳና ወይም ቆርኬ ጥቃት አጠያያቂ እንደኾነ ነው


የኢትዮጵያ ካርታ
የኢትዮጵያ ካርታ

ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም.፣በታጣቂዎች ተፈጸመ በተባለ ጥቃት፣ ነዋሪዎቿ ለግድያ፣ የተረፉትም ለመፈናቀል እና ለንብረት ዝርፊያ የተዳረጉባት አውራ ጎዳና ወይም ቆርኬ፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ እና በዐማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አዋሳኝ ላይ የምትገኝ መንደር ናት፡፡

በዐማራ ክልል በኩል፣ መንደሯ የክልሉ አካል እንደኾነች ጠቅሰው “አውራ ጎዳና” ሲሏት፤ በኦሮሚያ ክልል በኩል ደግሞ፣ መንደሯ የኦሮሚያ ክልል መኾኗን ጠቅሰው “ቆርኬ” ይሏታል።

በዚኽች መንደር፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ፣ በዐማራ ክልል በኩል የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ባለሥልጣንና በጥቃቱ የተፈናቀሉ ነዋሪዎቿ፣ “የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኀይል” እንደኾነ ይናገራሉ።

በኦሮሚያ ክልል የፈንታሌ ወረዳ ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ደግሞ፣ የኢትዮ-ጅቡቲ መሥመርን ለመቆጣጠር ዝተዋል፤ ያሏቸው የፋኖ ታጣቂዎች፣ በመንደሯ ላይ በማነጣጠር በመከላከያ ኀይሉ እና በኦሮሚያ ፖሊስ ላይ ጥቃት እንደከፈቱና ይህም ለችግሩ መነሻ እንደኾነ ያስረዳሉ፡፡

የአወዛጋቢዋ አውራ ጎዳና ወይም ቆርኬ ጥቃት አጠያያቂ እንደኾነ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:13:32 0:00

በታጣቂዎቹ እና ተባባሪዎቻቸው ናቸው ባሏቸው የመንደሯ ነዋሪዎች ላይ፣ የሕግ ማስከበር ርምጃ እንደተወሰደና ተዘግቶ የነበረው መንገድም እንደተከፈተ፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ ገልጸዋል፡፡

በጥቃቱ በርካታ የመንደሯ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች አካባቢዎች እንደተፈናቀሉ የሚናገሩት ተጎጂዎች በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት በችግር ላይ እንደሚገኙና የደረሰላቸውም አካል እንደሌለ አመልክተዋል፡፡

ሁለቱ ክልሎች በይገባኛል የሚወዛገቡባትና ከዐዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ የምትገኘው ይህች መንደር፣ በዐማራ ክልል በኩል “አውራ ጎዳና” እየተባለች እንደምትጠራና በአሁኑ ወቅት ክልሉ የገነባቸውና የሚያስተዳድራቸው መሠረተ ልማቶች እንዳሏት፣ ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች አስረድተዋል፡፡

በአንጻሩ በኦሮሚያ ክልል በኩል፣ “ቆርኬ” የምትባለው መንደሯ፣ በፈንታሌ ወረዳ በጡጡጥ ቀበሌ ሥር ያለች፣ የገዳ ሥርዐት አካል የኾነው ‘ጅላ’ የሚፈጸምባት ታሪካዊ መንደር እንደኾነች የወረዳው ተወላጆች ገልጸዋል፡፡ በዐማራ ክልል አስተዳደር ሥር ናት መባሏንም፣ “ከወሰን ውጭ በሰሜን ሸዋ ውስጥ በመካለሏ” እንደኾነ ተችተዋል፡፡

የይገባኛል ውዝግቡንና የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ፣ ከዐማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ እንዲሁም ከምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አመራሮች አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን አልቻለም፡፡ በዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም አላነሡልንም፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪዎች የእጅ ስልክ ደግሞ በደወልንላቸው ሰዓት ጥሪ አይቀበልም፡፡

ኾኖም፣ ከአንድ ዓመት ከአራት ወራት በፊት፣ በዚኹ አካባቢ ተመሳሳይ ግጭት በተነሣበት ወቅት ከአሜሪካ ድምፅ የተጠየቁት፣ የዐማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የኮሙኒኬሽን መምሪያ ሓላፊ የነበሩት መሐመድ አሕመድ፣ “ቆርኬ” የሚባል ስያሜ ከየት እንደመጣ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ “አሞራ ቤት” እየተባለች በምትጠራው ቀበሌያቸው ሥር ግን፣ “አውራ ጎዳና” ተብላ የምትጠራው መንደር እንዳለች ተናግረው ነበር።

በዐማራ ክልል በኩል ከአነጋገርናቸው የበዙት ነዋሪዎች፣ ጥቃቱ የተፈጸመው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኀይል አባላት ባሏቸው የመንግሥት ታጣቂዎች እንደኾነ ቢገልጹም፣ የታጣቂዎቹን ማንነት አስመልክቶ፣ ከሌላ ሦስተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም።

ኾኖም፣ የኦሮሚያ ክልል እና የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በሰጧቸው መግለጫዎች፣ የኦሮሚያ ክልልም ኾነ የሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይሎች መፍረሳቸውንና አባላቱም ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች በዳግም አደረጃጀት መግባታቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ምላሽ ለማግኘት፣ በእጅ ስልካቸው ላይ ደውለን ያደረግነው ጥረት አልተሳም። እንዲህ ዓይነት በወሰን ላይ የሚነሡ የይገባኛል ውዝግቦችን አስመልክቶ ምላሽ ለማግኘት በፌደሬሽን ምክር ቤት በቢሮ ስልክ ደውለን ነበር አልተሳካልንም።

በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በአካባቢው ስለተፈጠረው ችግር ጥቆማዎች እንደደረሱትና የምርመራ ሥራ ለማከናወን መረጃዎችን እያሰባሰበ እንደሚገኝ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG