በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሰሜን ሸዋ ዞን የአውራ ጎዳና መንደር ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን ነዋሪዎች ገለፁ


በሰሜን ሸዋ ዞን የአውራ ጎዳና መንደር ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን ነዋሪዎች ገለፁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:27 0:00

በሰሜን ሸዋ ዞን የአውራ ጎዳና መንደር ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን ነዋሪዎች ገለፁ

በዐማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አውራ ጎዳና ወይም ቆርኬ ከተማ ላይ፣ የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ፈጽመውታል ባሉት ጥቃት፣ ሰላማዊ ዜጎች እንደተገደሉና ከቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት እና ተጎጂዎች አስታወቁ፡፡

በ“ኦሮሚያ ልዩ ኀይል” እንደተፈጸመ በገለጹት ጥቃት፣ ከዐዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ በሚወስደው አውራ ጎዳና ዳር የምትገኘዋ ከተማ ነዋሪዎች ንብረት እንደተዘረፈና እንደወደመ፣ በሕይወት የተረፉትም እንደተፈናቀሉ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

በዐማራ ክልል በኩል፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የመስኖ እና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ሲራጅ አሊዬ አደም፣ ችግሩ የተከሠተው፣ ከትላንት በስቲያ እሑድ፣ “የኦሮሚያ ልዩ ኀይል አባላት፣ በከተማው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ነው፤” ብለዋል፡፡

ይኸውም፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ በድንገት አካባቢውን ለቀው ከወጡ ከአንድ ቀን በኋላ እንደኾነ፣ አቶ ሲራጅ አስረድተዋል፡፡በጥቃቱ፣ ቢያንስ 10 ሰዎች እንደተገደሉ፣ ሓላፊው ተናግረዋል።

ከአነጋገርናቸው ውስጥ የበዙት ነዋሪዎች፣ ጥቃቱ የተፈጸመው "የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኀይል አባላት" ባሏቸው የመንግሥት ታጣቂዎች ሲኾን፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እንደዚኹም የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት፣ በተለያዩ ጊዜያት በሰጧቸው መግለጫዎች፣ የኦሮሚያ ልዩ ኀይል መፍረሱንና አባላቱም ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች በዳግም አደረጃጀት እንደገቡ ገልጸዋል። በነዋሪዎቹ የተገለጹትን ታጣቂዎች ማንነት አስመልክቶ፣ ከሌላ ሦሰተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም።

ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት እና በተከተለው ችግር ላይ፣ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ፣ ከምሥራቅ ሸዋ ዞን ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ እንዲሁም ከፈንታሌ ወረዳ አስተዳዳሪ፣ የበኩላቸውን ምልከታ እና ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

በኦሮሚያ ክልል ከምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ጋራ የምትዋሰነው አውራ ጎዳና ወይም ቆርኬ ተብላ በምትታወቀው በዚኽች አነስተኛ ከተማ እና በዙሪያዋ ካለው የጸጥታ ኹኔታ ጋራ በተያያዘ፣ የዐማራ እና የኦሮሚያ ክልል አስተዳደሮች ውዝግብ ውስጥ የገቡበት አጋጣሚ እንደነበር ይታወሳል። ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG