በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

15ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ በካምፓላ


"እናንተ መሪዎች የሆናችሁት በእነዚያ ሴቶችና በሕፃናቱ ምክንያት ነው፡፡ እናንተን ሥልጣን ላይ ያስቀመጧችሁ ሰዎች ናቸው - እነርሱ፡፡ እንደ አንዲት አፍሪካዊት ሴት እና የአራት ልጆች እናት ማለት የምፈልገው ይህቺ አፍሪካ፣ የሚኖሩባት ሰዎች ሁሉ መሆኗን ነው፡፡ አፍሪካ ከባርነት ማነቆዎቿ ተላቅቃለች፤ ነፃነታችንንም ጨብጠናል፡፡ እና ታዲያ፣ በፃነት ማለት ምን ማለት ነው? በፃነት ማለት፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ውኃ፣ ንፅሕና ማለት ነው፡፡ ጤና ደግሞ ኃብት ነው፡፡"

- አርቲስት ዩቮን ቻካ ቻካ ለአፍሪካ መሪዎች ከተናገረችው የተወሰደ፡፡

የአፍሪካ ሕብረት 15ኛ የመሪዎች ጉባዔ በሶማሊያ አክራሪ አማፂያን ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ሊወሰድ በሚችልበት ሁኔታና በአህጉሪቱ የሴቶችና የሕፃናት ጤና ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመወያየት ላይ ነው፡፡ ለምን የአሕጉሪቱ እናቶች በወሊድ ምክንያት እንዲህ በብዛት ይሞታሉ? የሚል ጥያቄም ተስቷል፡፡

ጉባዔው ትናንት በዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ውስጥ ሲከፈት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የድጋፍ መልዕክትም በመልዕክተኛቸው ቀርቧል፡፡

"ከካምፓላ ወጣ ብለው ጉባዔ የተቀመጡት ከሰላሣ በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ መሪዎች በተደባለቀ መንፈስ፣ በደስታና በኀዘን ይወያያሉ" ይላል ከዩጋንዳ የመጣው ዘገባ፡፡ አንድም አፍሪካ የዓለምን የእግር ኳስ ዋንጫ በተሣካ ሁኔታ ማስተናገዷ የደስታቸው ምንጭ ሆነ፤ ደግሞም ይህንኑ ጨዋታ ሲመለከቱ አልሻባብ ባደረሰው የቦምብ ጥቃት የተገደሉ 76 ዜጎቻቸውና አድራጎቱም አበሳጫቸው፡፡

ጥቃቱ በምድራቸው የተፈፀመው የ15ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ አስተናጋጁ የዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በሶማሊያ የሚገኙትን አክራሪ አማፂያን በጦር ኃይል ለማስገበር ዝተዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሶማሊያ ውስጥ ለሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ለአሚሶምና ለካምፓላው ጥቃት ምርመራ ያላቸውን ጠንካራ ድጋፍ በመልዕክተኛቸው በጠቅላይ አቃቤ ሕጉ በኤሪክ ሆልደር አማካይነት አስታውቀዋል፡፡

የመሪዎቹ ጉባዔ ከሶማሊያና የሽብር ጉዳይ ወጣ ብሎም በጤና ጥበቃው መስክ በተለይ በሴቶችና በሕፃናት ጤና ጉዳይ ላይ ተነጋግሯል፡፡

ጉባዔው ሰኞ ዕለት በዝግ ሲወያይ የዋለ ሲሆን ከተነሱት ጉዳዮች መካከል ለመጭው የካንኩን - ሜክሲኮ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የጋራ አቋም መያዝና በሊብያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ የተባበሩት መንግሥታት አንድ መንግሥት ምሥረታ ጉዳይ እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡

XS
SM
MD
LG