የህብረቱ የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ሱዳንን ማገዱን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የሱዳን ተቃውሞ መሪዎች ገዢው የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤት ስለሀገሪቱ የወደፊት የፖለቲካ ዕጣ እንደራደር ብሎ ያቀረበላቸውን ጥሪ ውድቅ እድርጓል።
በዚሁ ሳምንት ውስጥ ካርቱም ላይ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የተገደሉበትና የቆሰሉበት ዕርምጃ ተወስዶ ሲያበቃ እንነጋገር ብሎ ጥሪ ከልብ የመጣ አይደለም ብለዋል። ዕማኞች እንደተናገሩት ጥቃቱን ያደረሱት ያጣዳፊ ድጋፍ ኃይሎች የተባለው ሚሊሽያ ነው ።
የተቃዋሚው ጎራ ደጋፊ የሆኑ ሃኪሞች እንደገለፁት በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ በደረሰው ጥቃት የተገደለው ሰው ብዛት ከትናንት ረቡዕ ወዲህ ወደ አንድ መቶ ሁለት ከፍ ብሏል።
የሱዳን የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ደግሞ የሞቱ ሰዎች ከአርባ ስድስት አይበልጡም ሲል ተናግሯል።
የሱዳን ባለሙያዎች ማኅበር ቃል አቀባይ መሃመድ ዩሴፍ አል ሙስታፋ በሰጡት ቃል “የጄኔራል አብደልፋታህ ቡርሃን የእንደራደር ጥሪ ከምር አይደለም። በሥራቸው ያሉ ናቸው እኮ ሰው የገደሉት መግደልም የቀጠሉት” ብለዋል።
ተቃዋሚዎቹን የሚወከለው የነፃነት እና የለውጥ ኃይሎች የተባለው አካል ጦር ሰራዊቱ ሥልጣኑን ለሲቪሎች እንዲያስረክብ ግፊት ለማድረግ ዘመቻውን ይቀጥላል ነው ያሉት አል ሙስታፋ።
የገዢው የሽግግር ወታደራዊ ምክር ቤት መሪ ጄኔራል ቡርሃን ትናንት በሰጡት መግለጫ ነው ያለምንም ገደብ ሲሉ በጠሩት አኳሃን ከተቃዋሚ መሪዎች ጋር ድርድሩን ለመቀጠል ዝግጁ ነን ብለዋል።
ጄኔራሉ ጨምረው ለስምንት ሳምንታት በካርቱም በመከላከያ ሚኒስቲሩ ደጃፍ የቀጠለውን የመቀመጥ ተቃውሞ ደም ባፋሰሰ ዕርምጃ የበተኑት በተጠያቂነት ይያዛሉ ብለዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ