ሶማሊያ በሀገሯ የሚገኘው ሰላም አስከባሪ ኃይልን የማስወጣቱ ሂደት ለሦስት ወራት እንዲዘገይ ያቀረበችው ጥያቄ በአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክርቤት መፅደቁን፣ በሶማሊያ የሚገኘው የህብረቱ ልዑክ ኃላፊ መሐመድ ኤል-አሚን ሱኤፍ ለአሜሪካ ድምፅ አረጋግጠዋል።
ሱኤፍ ሰኞ ማታ ከአሜሪካ ድምፅ የሶማሌ ቋንቋ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ሶማሊያ የጸጥታ ኃላፊነቶችን ከአፍሪካ ህብረት ኃይሎች ለመረከብ "ፖለቲካዊ ፍላጎት" እንዳላት ገልፀው፣ የሶማሊያ ጦር ግን ገና በመደራጀት ላይ ያለ አዲስ ጦር በመሆኑ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የመደገፍ፣ የማሰልጠን እና የማስታጠቅ ሃላፊነት አለበት ብለዋል።
የሶማሌ መንግስት "ለዘላለም መታገዝን አይፈልግም፣ ኃላፊነት መውሰድ ይፈልጋል" ያሉት ሱኤፍ መንግስቱ "ሰብዓዊ መብትን፣ የህግን የበላይነት እና ዲሞክራሲን" እያራመደ ነው ብለዋል።
ሱኤፍ አክለው፣ አል-ሻባብ ያለውን አቅም አሳንሰን አናይም" ያሉ ሲሆን፣ "አል-ሻባብ አሁንም የሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች እንዳሉ፣ ምንጩ ባይታወቅም የጦር መሳሪያዎችን እንደሚያገኙ እና በአግባቡ መታጠቃቸውን እንደሚረዱ ገልፀዋል። ነገር ግን በጋራ ጥረት በማድረግ አልሻባብን ማዳከምና ማሸነፍ እንችላለን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ከሶማሊያ ለቆ በሚወጣበት ጊዜ፣ ወታደሮቻቸውን ያዋጡ ሀገራት፣ መሳሪያዎቻቸውን፣ ተሽከርካሪዎቻቸውን እና ጠመንጃዎቻቸውን ለሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ለመለገስ መስማማታቸውን ሱኤፍ አመልክተዋል።
ሶማሊያ ለአስርት ዓመታት በዘለቀ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ምክንያት አሁንም ጦሯን ለማጠናከር ትግል ላይ መሆኗን ያመለክቱት ሶኤፍ፣ ሶማሊያ የጦር መሳሪያዎችን መግዛት እንድትችል፣ እ.አ.አ በ1992 የተጣለበት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መነሳት አለበት ብለዋል።
መድረክ / ፎረም