በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ደረጃዎችን እንዲተገብር ተጠየቀ


ሞሪታንያ ዋና ከተማ ኑአክሸት ውስጥ ለተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 31ኛ የመሪዎች ጉባዔ ድጋፏን እንደምትሰጥ ዩናይትድ ስቴትስ አስታወቀች። ይህንን የሃገራቸውን መልዕክት ያስተላለፉት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ሄዘር ኑወርት ትናንት ባወጡት መግለጫ ነው።

የአፍሪካ ኅብረት በመጭዎቹ ዓመታት ውስጥ አካባቢያዊ እክሎችን ለመፍታት በሚያስችለው አቋም ላይ ይገኝ ዘንድ እንደሚያግዘው እምነታቸው መሆኑን የገለፁበትን “ኅብረቱ የያዘውን የመለወጥ ጥረት የኑአክሸቱ ጉባዔ ማጠናከሩ ዩናይትድ ስቴትስ የምትደግፈው ሂደት ነው” ብለዋል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ሄዘር ኖወርት።

ለአፍሪካ ኅብረት ሰላምና ፀጥታ ቀዳሚ ጉዳዮች መሆናቸውን የኑአክሸቱ የመሪዎች ጉባዔ በአፅንዖት መመልከቱን አጉልቶ ያነሣው የቃል አቀባይዋ መግለጫ በመላ አኅጉሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ የተያዘውን አፍሪካዊ ጥረት ዩናይትድ ስቴትስ እንደምታደንቅ አስታውቋል።

የአፍሪካ ኅብረት በዓለም እጅግ አደገኛ በሆኑ አካባቢዎችና ሁኔታዎች ውስጥ ሰላም አስከባሪዎቹን እያሠማራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አመልክቶ ለኅብረቱ ግጭቶችን የመፍታት ጥረቶች፣ የአፍሪካዊያኑን አቃቢያነ-ሰላምና እነርሱም የሚጠብቋቸውን ሕዝቦች ደኅንነትም ለማረጋገጥ እጅግ ከፍ ያሉ የግዳጅ አፈፃፀም ደረጃዎችን ማውጣት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አሳስቧል።

“የፋይናንስ ግልፅነትንና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ደረጃዎችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ እንደሚወስድ እንገነዘባለን፤ እነዚህን ግቦች ለመጨበጥ በተያዘው ጥረትም በምናደርገው የማይቋረጥ ትብብር እንገፋለን” ይላል በፅሁፍ የወጣው የኖወርት መግለጫ።

የአፍሪካ ኅብረት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ከመጠየቁ በፊት የእነዚያን ደረጃዎች ለሰላም ጥበቃ ድጋፍ በሚሰጥባቸው ዘመቻዎቹ ሁሉ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረጋቸውን እንዲያረጋግጥም የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መክሯል።

ለአፍሪካ ኅብረት የማረጋጋት ዘመቻዎች አስተማማኝ የገንዘብ ፍሰት አሠራሮች መኖራቸው ለስኬታማነታቸው አስፈላጊ መሆናቸውን ዩናይትድ ስቴትስ እንደምትገነዘብ ያስታወቀው ይኸው መግለጫ ኅብረቱ እራሱን በገንዘብ የሚደግፍባቸው ጥረቶች ማደግ እንዳለባቸውና ለሰላም ፈንዱም መዋጮዎች መደረግ እንደሚኖባቸው አሳስቧል።

የኅብረቱን የሰላም ፈንድ ከፍተኛ ተጠሪ ዶ/ር ዶናልድ ካቤሩካና የኅብረቱን የሰላምና የፀጥታ ኮሚሽነር ኢስማኢል ቼሩጊ ለአፍሪካ ኅብረት ሊደረግ የሚችለውን የገንዘብ ድጋፍና ለውጦችንም አስመልክቶ ፍሬያማ ንግግሮችን ለማድረግ ወደ ዩናይትዩ ስቴትስ የሚያርጉትን ጉዞ ሃገራቸው በጉጉት እንደምትጠብቅ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ሄዘር ኖወርት አስታውቀዋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ

የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ደረጃዎችን እንዲተገብር ተጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:40 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG