በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ኅብረት በትግራይ ክልል ተዋጊዎችን ማሰናበት እና መልሶ ማዋሐድ በአፋጣኝ እንዲተገበር አሳሰበ


የአፍሪካ ኅብረት በትግራይ ክልል ተዋጊዎችን ማሰናበት እና መልሶ ማዋሐድ በአፋጣኝ እንዲተገበር አሳሰበ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:59 0:00

- የሰላም ስምምነቱን አተገባበር ገመገመ፤ የክትትል እና ቁጥጥር ቡድኑን ቆይታ አራዘመ

በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ “የትግራይ ተዋጊዎች ኃይል” የተባለውን ታጣቂ አደረጃጀት የማፍረስ ሒደት እና ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ኑሮ መልሶ የማዋሐድ፣ እንዲሁም ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራዎች፣ በአስቸኳይ ሊተገበሩ እንደሚገባ፣ የአፍሪካ ኅብረት አሳሰበ፡፡

አህጉራዊ ኅብረቱ፣ በፌዴራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል፣ ባለፈው ጥቅምት ወር በፕሪቶርያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ትግበራ ሒደት መገምገሙን፣ በአወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡በጉዳዩ ላይ፣ የትግራይ ክልል የኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤትንና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርን አስተያየት ጠይቀናል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት በእና በህወሓት መካከል፣ ባለፈው ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ-ፕሪቶርያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ትግበራ ሒደት የሚከታተለው እና የሚቆጣጠረው የአፍሪካ ኅብረት ቡድን፣ ትላንት ረቡዕ፣ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከህወሓት እንዲሁም ከኢጋድ ተወካዮች ጋራ በመኾን፣ አፈጻጸሙን መገምገሙን፣ የአፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል::

በዘላቂነት ተኩስ የማቆም ስምምነቱ መሠረት፣ የትግራይ ተዋጊዎች ከባድ ትጥቆችን እንደፈቱ፣ ቀላል እና መካከለኛ ትጥቆችን ደግሞ በማስረከብ ሒደት ላይ እንዳሉ መግለጫው አመልክቷል፡፡

በትግራይ ክልል፥ ያልተገደበ ሰብአዊ ርዳታ እንዲገባ ማመቻቸት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች ማለትም የጤና፣ የትራንስፖርት፣ የንግድ እንቅስቃሴ መጀመር እና የትምህርት ቤቶች በአብዛኛው የክልሉ አከባቢዎች ዳግም መከፈት የሚሉት፣ በጋራ ግምገማው በአዎንታዊነት መጠቀሳቸውን መግለጫው ጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል፣ በጦርነቱ ወቅት፣ በትግራይ ክልል የነበረውን የተዋጊዎች አደረጃጀት ማፍረስ እና ወደ ሰላማዊ ኑሮ መልሶ የማደራጀት ሥራው፣ በአፋጣኝ መተግበር እንዳለበት የጋራ ግምገማው ማሳሰቡን መግለጫው አመልክቷል፡፡

ነገ ዐርብ፣ ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ የሰላም ስምምነቱ ፈራሚ የኾነው ህወሓት፥ የተዋጊዎቹን፣ የመካከለኛ እና ቀላል የጦር መሣርያዎች፣ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደሚያስረክብና ተዋጊዎቹን የማሰናበት ሥራ ደግሞ በይፋ እንደሚጀመር ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት በመጠበቅ ረገድ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለሱ ሥራም እንዲተገበር፣ የአፍሪካ ኅብረት በመግለጫው አሳስቧል፡፡

የትግራይ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም፣ በሰላም ስምምነቱ መሠረት፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ከመመለሳቸው አስቀድሞ፣ የውጭ ወታደሮች እና የኢትዮጵያ መከላከያ ያልኾኑ ኃይሎች፣ ከክልሉ መውጣት ይገባቸዋል፤ ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ያወጣውን መግለጫ አስመልክቶ ማብራርያ የሰጡን፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ገብረ መድኅን ገብረ ሚካኤል፣ የትጥቅ መፍታቱ እና ተዋጊዎችን በትኖ ወደ ቀድሞ ሕይወት የመመለሱ ሥራ፣ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ አኳያ፣ ጊዜ የሚወስድ ተግባር እንደኾነ ጠቅሰው፣ በፕሪቶርያው ስምምነት አተገባበር ግን፣ “ሒደቱ እየተቀላጠፈ ነው፤” በማለት ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫ፣ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች፣ መሠረታዊ ሕዝባዊ አገልግሎቶች ተጀምሯል፤ የተባለው፣ “የተጋነነ አገላለጽ ነው፤ ገና ብዙ መሥራት ያስፈልገዋል፤” ብለዋል፣ አቶ ገብረ መድኅን፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ የሰላም ስምምነት ሂደቱ እንዳይደናቀፍ ፣ በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ያሏቸውንም ጉዳዮች አንሥተዋል፡

የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት ትግበራ የሚከታተለውና የሚቆጣጠረው ቡድን፣ ሥራው፥ እስከ ታኅሣሥ 2023 እንዲቀጥልም፣ በትላንትናው ዕለት መወሰኑን፣ የኅብረቱ መግለጫ አስታውቋል፡፡

በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት፣ “ለኣፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚለው አህጉራዊ መርሕ መሠረት፣ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ እያሳዩ ለሚገኙት ተነሣሽነት እና ትብብር፣ ኅብረቱ በመግለጫው አመስግኗል፡፡

XS
SM
MD
LG