በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሰላም ስምምነቱን የሚከታተለው የአፍሪካ ኅብረት የጋራ ኮሚቴ ሶስተኛ ስብሰባ አካሄደ


የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ የተደረገውን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም የሚከታተለው የአፍሪካ ኅብረት የቁጥጥር እና የክትትል የጋራ ኮሚቴ ሶስተኛ ስብሰባ ባለፈው ዓርብ መካሄዱን ከኅብረቱ የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ የፊዴራል መንግስት እና የህወሓት ተወካዮች፣ እንዲሁም የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሉሲጉን ኦባሳንጆን ጨምሮ፣ የኅብረቱ ከፍተኛ ኮሚቴ ተወካዮች እንደተገኙ መግለጫው ጨምሮ አመልክቷል።

የጋራ ኮሜቴ ስብሰባው፤ ሁለቱም ወገኖች የሰላም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር በድጋሚ ቃል የገቡበት፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተን እና እንደገና ወደ ሲቪል ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበትን ሂደት፣ እንዲሁም ተፈናቃዮችን እንደገና የማስፈሩ ሂደት እንዲፋጠን የተስማሙበት እንደነበር ተገልጿል።

በተጨማሪም፤ በሰላም ስምምነቱ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ፣ የፖለቲካ ውይይት አስፈላጊነት ላይ የተስማሙበት እና የጋራ ኮሚቴው ስትራቴጂካዊ አካሄዱን የሚገመግምበት ስብሰባ ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ የተስማሙበት እንደነበር መግለጫው አትቷል።

ስብሰባው ከዚህም ሌላ፣ የጋራ ኮሚቴው የሥራ ዘመን እስከ ሚቀጥለው ዓመት ታህሣስ ወር ድረስ እንዲራዘም ወስኗል።

በሰላም ስምምነቱ መሠረት የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተን እና እንደገና ወደ ሲቪል ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበትን ፕሮግራም ለመደገፍ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ ከኅብረቱ የሠላም ፈንድ ላይ አንድ ሚሊዮን ዶላር እንዲሰጥ መወሰናቸውን የጋራ ኮሚቴው በምስጋና ተቀብሏል።

ኢትዮጵያ እና ህዝቧ ዘላቂ ሠላም ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት መደገፉን እንደሚቀጥል ያስታወቀው ኅብረቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ‘ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ’ በሚል መንፈስ ላሳዩት ቁርጠኝነት እንዲሁም ሌሎች የሠላም ሂደቱን ይደግፋሉ ያላቸውን መንግሥታት እና አካላት አመስግኗል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG