የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ቡርኪና ፋሶ ዋና ከተማ ኡዋጋ ዱጉ ላይ እንደሚካሄድ ኅብረቱ አስታወቀ፡፡
ከጉባኤው ጎን ኢቦላን ለመከላከል የገቢ ማሰባሰብያ መርሃግብር መዘርጋቱንም ኅብረቱ ይፋ አድርጓል።
ሰው ላይ ገና ያልተሞከረውና ደኅንነቱ፣ ፍቱንነቱና ፈዋሽነቱ ገና ያልተረጋገጠው የኢቦላ መድኃኒት ሕክምና ላይ መዋሉን እንደሚደግፍም ኅብረቱ ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ኬንያ ቀጣይዋ የኢቦላ መከሰት አብዝቶ የሚያሰጋት ሃገር እንደሆነች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት - WHO ባወጣው ሪፖርት ምንም እንኳ እስከአሁን ኢቦላ ቫይረስ ኬንያ ውስጥ ስለመገኘቱ መረጃ ወይም የደረሰው ጥቆማ ባይኖርም ሃገሪቱ በአካባቢው ግዙፏ የትራንስፖርት መናኸሪያ በመሆኗ ምክንያት የመጋለጧ ዕድልም የዚያኑ ያህል የሰፋ መሆኑን ገልጿል፡፡
ድርጅታቸው ኬንያን ለኢቦላ መከሰትና መዛመት ሁለተኛ ደረጃ የአደጋ ቀጣና አድርጎ የፈረጃትና የሚከታተላትም መሆኑን ናይሮቢ የሚገኙት የዓለም የጤና ድርጅት ተጠሪ ዶ/ር ኩስቶዲዮ ማንድላት ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል፡፡
“የምዕራብ አፍሪካው የኢቦላ ወረርሽኝ የዓለም ሥጋት የሆነ ከባድ የሕብረተሰብ ጤና ችግር ነው፡፡ በአጭር ጊዜ የሠራነው የአደጋ ሥጋት አካባቢዎች ትንታኔ ኬንያ የመተላለፉ ከፍተኛ ተጋላጭ ሆና አግኝተናታል፡፡ በመሆኑም ቫይረሱ እንዳይገባ፣ ወይም ከገባም ምላሻችን ፈጣን እንዲሆን መዘጋጀት በጣም አስፈላጊ ነው” ብለዋል ሐማንድላት፡፡
በሃገሪቱ የመግቢያ ጣቢያዎች ላይ ያለው ፍተሻ በጣም ደካማ መሆኑን የኬንያ ጋዜጦች መንገደኞችን እያነጋገሩ እየዘገቡ ነው፡፡
መንግሥት ግን በሽታውን ለመከላከል እየጣረ መሆኑን የሃገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጄምስ ማቻሪያ አስታውቀዋል፡፡
“ሚኒስቴሩ ብዙ መሥሪያ ቤቶች የሚሣተፉበት የኢቦላ ግብረኃይል አቋቁሟል፡፡ ኮሚቴው ላለፉት ሦስት ወራት እየተሰበሰበ በየቀበሌውና በመላ ሃገሪቱም እንዲሁም በዓለምአቀፍ ደረጃ ያለውን ሁኔታ እየተከታተለ ለሚኒስትሩም መወሰድ የሚገባቸውን እርምጃዎች እያማከረ ነው” ብለዋል፡፡
ኬንያ ለአሁን ነፃ ነች ቢባልም ሥጋቱ ግን አይሎ እንዳጠላባት ነው፡፡
ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡