አማራ ክልል ውስጥ ወደ ተኩስ የዘለቁት የመከላከያ ሠራዊትና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ በአፋጣኝ አቁመው ለሰላማዊ ውይይት እንዲቀመጡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጥሪ አቅርበዋል።
የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ትናንት፣ ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ተፋላሚዎቹ ለሲቪሎች ደኅንነት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና የዓለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ባልደረቦች የሆኑ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ሁለት ምሁራን የአፍሪካ ኅብረት ያቀረበው የሰላም ውይይት ሃሳብ “ሊደገፍ ይገባል” ብለዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ያያው ገነት ቸኮል በሰጡት አስተያየት፤ “መንግሥት ከሰላም ውይይቱ አስቀድሞ ‘ግጭቱን ያነሳሱና ያባባሱ ነባርና የወቅቱ የሕዝብ ጥያቄዎች’ - ሲሉ የገለጿቸውን - ‘የጥቂት ሥልጣን ፈላጊ ቡድኖች’ ከሚል ፍረጃው መታረም ይኖርበታል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በያዝነው ሣምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት የምሥራቅ አፍሪካ የጋራ ልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ)፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ‘ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ’ ሲል የጠራቸው አማራ ክልል ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎችና በመንግሥት መካከል የውይይት መድረክ እንዲያመቻቹና እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ለዝርዝሩ የተያያዘውን ዘገባ ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም