በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አፍሪካ ህብረት ፑቲን ግጭቱን እንዲያቆሙ አሳሰበ


የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት የሴነጋሉ ፕሬዚዳን ማኪ ሳል የሩሲያውን ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ይፈልጋሉ፡፡ ማኪ ሳል ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር የተነጋገሩት ሴነጋል በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያውን ወረራ በማወገዝ ባስተላለፈው ድምፅ ላይ አገራቸው ሴነጋል ድምጸ ተአቅቦ ባደረገችበት ሳምንት ነው፡፡

የቪኦኤ ዘጋቢ አኒካ ሃምርስካልግ ከዳካር እንደዘገበችው የአፍሪካ አገሮች ጦርነቱ እንዲያበቃ ይፈልጋሉ ይሁን እንጂ ደግሞ ፕሬዚዳንት ፑቲንንም ማበሳጨትም አይሹም፡፡

በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነታቸው የሴነጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ትናንት ረቡዕ ያቀረቡት ጥያቄ ከሳምንት በፊት በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ የሩሲያን ወረራ ባለማውገዝ ድምጸ ተአቅቦ ካደረጉ 16 አገሮች አንዷ ከሆነችው የራሳቸው ሴነጋል አቋም የተለየ ነው፡፡

በአፍሪካ የዴሞክራሲ አርአያ ሆና በምትታወቀው አገር ይህ መሆኑ ብዙዎችን ያስገረመ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በአፍሪካ የስትራቴጂክል ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ጆሴፍ ሴግል “ሴኔጋል በመንግሥታቱ ድርጅት ያሳየቸው አቋም እንደ ለሌሉች በርካታ አፍሪካ አገሮች ለዓመታት ሲታይ የኖረ የገለልተኝነት አቋም የታየበት እንጂ ለሩሲያ የተሰጠ ድጋፍ አይደለም፡፡” ይላሉ፡፡

አፍሪካ ህብረት ፑቲን ግጭቱን እንዲያቆሙ አሳሰበ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:03 0:00

አፍሪካውያኑ በሃያላን አገሮች ጠብ መግባት አይፈልጉም የሚሉት ጆሴፍ “ገለልተኝነት ለመጠበቅ የተወሰደ አቋም ነው፡፡” ብለዋል፡፡

እንዲህ ብለዋል ጆሴፍ

“ ሩሲያ አፍሪካ ውስጥ ትልቅ የንግድ ልውውጥ አላት፡፡ ለምሳሌ ሉክ ኦይል የተሰኘው የሩስያ ነዳጅ ኩባንያ ባላፈው ዓመት ከሴነጋል ጋር የ300 ሚሊዮን ዶላር ኮንትራት ተፈራርሟል፡፡ ይኸው የሩሲያ ኩባንያ በካሜሩን ግብጽ ጋና እና ናይጄሪያ ውስጥ ይሠራል፡፡ የሩስያ ማዕድን ድርጅቶች በአፍሪካ ይሳተፋሉ፣ በአንጎላ አልማዝ፣ በጊኒ አልሙኒየም፣ በናሚቢያ ዩራኒየም ያወጣሉ፡፡”

ከሁሉም በላይ ሞስኮ ለአፍሪካ የጦር መሳሪያዎችን በማቅረብ ትታወቃለች፡፡ እኤአ ከ2015 ጀምሮ ከ20 በላይ ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች ጋር ወታደራዊ ስምምነቶች ተፈራርማለች፡፡

ለክሬምሊን ቅርበት ያላቸው የሩሲያ የግል ወታደራዊ ኩባንያዎችም እንደ ማሊ እና ማዕከላዊ አፍሪካ በመሳሰሉ አገሮች አፍሪካ ውስጥ ስር የሰደደ ጠንካራ መሰረት አላቸው፡፡

በበርካታ አፍሪካ አገሮች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያለ ስለሆነም አፍሪካውያኑ አገሮች ከክሬሚሊን ጋር መጋጨት አይፈልጉም፡፡ ጦርነቱ ሄዶ ሄዶ በራሳቸው ላይ የሚያስከትለውንም ውጤት የአፍሪካ መሪዎች ከወዲሁ እያዩት ነው፡፡

በዳካር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ክፍለ ትምህርት ኃላፊ የሆኑት አብዱራህማን ታሂሚ እንዲህ ይላሉ

“ሩሲያ ብዙ ምርቶችን ወደ ውጭ የምትልክ አገር ናት፡፡ እነዚህ ደግሞ ጋዝ እና ጥሬ ዕቃዎችን ጨምሮ በምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉትን እንደ ስንዴ የመሳሰሉትን ምርቶች ናቸው፡፡”

ታሂሚ፣ “ጥሩነቱ የአፍሪካ ህብረት ድምጹን የሚያሰማበት መድረክ ግን አለው” ይላሉ

“ዓለም አቀፍ ግንኙነት በኃያላን አገሮች ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡የአፍሪካ ህብረት እኮ አህጉራዊ ተቋም ሲሆን በሚያሰማው ድምጽ ተጽዕኖ ሊያመጣ የሚችል ነው፡፡”

“ሩሲያም አፍሪካን ትፈልጋለች” ያሉት ታህሚ፣ ለራሷ ስትል የአፍሪካን ህብረት ማዳመጥ ይጠቅማታል ይላሉ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ጥሪን አስመልክቶ ክሬምሊን ባወጣው መግለጫ ወረራውን “ዶናባስን ለመከላከል በተደረገ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ሲል ጠቅሶታል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማኪ ሳል ስላቀረቡት የተኩስ አቁም ጥሪ ግን ምንም አላለም፡፡ ይልቁንም ሩሲያ የውጭ አገር ዜጎች በሰላም ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቧንና ሁለቱ መሪዎች የሩሲያና አፍሪካ ግንኙነት ለወደፊቱ የበለጠ ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን አስታውቋል፡፡

XS
SM
MD
LG