በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ወልድያ ውስጥና በአካባቢዋ ሕይወት የጠፋበት ግጭት ተፈጠረ


የአማራ ክልል ካርታ - ከተመድ የተገኘ
የአማራ ክልል ካርታ - ከተመድ የተገኘ

በግጭቶቹ ቢያንስ የስድስት ሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ የቆሰሉም እንዳሉ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉም እንደነበሩ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አቶ አዳነ ጥላሁን ለቪኦኤ ገልፀዋል።

በአማራ ክልል ወልድያ አካባቢና በሌሎችም ሥፍራዎች ከትናንት ጀምሮ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር የተፈጠሩ ግጭቶች እንደነበሩና አሁንም ውጥረት እንደነገሠ መሆኑ ተገለፀ።

በግጭቶቹ ቢያንስ የስድስት ሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ የቆሰሉም እንዳሉ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉም እንደነበሩ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አቶ አዳነ ጥላሁን ለቪኦኤ ገልፀዋል።

ግጭቱ የተፈጠረው ቅዳሜ ከቀትር በኋላ ወጣቶች መንግሥቱን የሚቃወሙ መፈክሮችን እያሰሙና እየዘፈኑ ሳሉ በአካባቢው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች እንዲያቆሙ ከጠየቋቸው በኋላ በተነሣ እሰጥ አገባ እንደነበረና ከዘጠኝ ሰዓት አካባቢ አንስቶ ተኩስ መከፈቱን አቶ አዳነ አመልክተዋል።

ማምሻውንም ቁጥሩ ከዚያ በላይ እንደሆነ ቢሰሙም ስድስት ሰው መገደሉን ማረጋገጣቸውንና ዛሬም በቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት ሌላ ግጭት መቀስቀሱን የመኢአዱ ዋና ፀሐፊ ጠቁመው ወደ ወልድያ የወረዱት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሁኔታውን ለማብረድ መጣራቸውንና ታስረው ያደሩ ሃያ ሰዎችን ማስፈታታቸውን ገልፀዋል።

በወቅቱ በተነሣ ሁከትም የትግራይ ተወላጅ በሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ሕንፃዎችና ሆቴሎች ላይም ጥቃት መፈፀሙንና የወደመም ንብረት መኖሩን አቶ አዳነ ተናግረዋል።

ከወልድያ ሌላም ሃራ፣ አዳጎ፣ ደብረ ገሊላና ጎንደር በር በሚባሉ አካባቢዎችም ሰልፎችና ግጭቶች እንደነበሩ መስማታቸውን የመኢአድ ዋና ፀሐፊ አክለው ጠቁመዋል።

የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውንና የክልሉን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁንን ለማግኘት ቪኦኤ ማምሻውን ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሣኩም።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ወልድያ ውስጥና በአካባቢዋ ሕይወት የጠፋበት ግጭት
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:19 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG