በምሥራቅ ኮንጎ ሰሜን ኪቩ ክፍለ ሀገር በርካታ መንደሮች ውስጥ፣ ቢያንስ 60 የሚኾኑ ሰዎች አስከሬኖች መገኘታቸውን፣ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡
የካሻሊ እና ካዛሮሆ መንደር ነዋሪዎች፣ ባለፉት በርካታ ቀናት ኤም23 በተባለው ቡድን ታጣቂዎች የተገደሉ መኾናቸውን፣ ቢትዋ የተባለ አካባቢ ምክትል አስተዳዳሪ አይዛክ ኪቤራ ተናግረዋል፡፡
በአመዛኙ በኮንጎ ቱትሲዎች የተቋቋመው ታጣቂ ቡድን፣ ሩዋንዳ አቅራቢያ የሚገኘውን ጎማን፣ ከ10 ዓመታት በፊት ተቆጣጥሮ ከነበረበት ጊዜ ወዲህ እየገነነ ሔዷል፡፡ ቡድኑ ራሱን ኤም23 ብሎ የሰየመው፣ እአአ በ2009 መጋቢት 23 ቀን ከተደረሰው የሰላም ውል በመነሣት ሲኾን፣ የኮንጎን መንግሥት፣ “ስምምነቱን አላከበረም፤” በማለት ይወነጅላል፡፡
ሽምቅ ተዋጊው ቡድን፣ ለዐሥር ዓመታት ገደማ አድፍጦ ከቆየ በኋላ፣ ከአንድ ዓመት በፊት እንደገና መንቀስቀስ ጀምሯል፡፡