በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በናይጄሪያ ምርጫን የሚዘግቡ 14 ጋዜጠኞች እስራት ጥቃትና ወከባ ደረሰባቸው - ሲፒጄ


ሲፒጄ
ሲፒጄ

በናይጄሪያ ምርጫን በመዘገብ ላይ የነበሩ 14 ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሠራተኞች እስራት ጥቃትና ወከባ ደርሶባቸዋል ሲል የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው ‘ሲፒጄ’ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

‘ዊኪታይምስ’ የተሰኘው የዜና ድህረ ገጽ ባለቤት ሃሩና ሳሊሱ ክስ ሳይመሠረትበት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በፖሊስ እገታ ውስጥ ይገኛል ሲል የድህረ ገጹ አዘጋጅ ያኩቡ ሞሃመድ ነግሮኛ ሲል ሲፒጄ በመግለጫው አመልክቷል። ፖሊስ ሳሊሱን ያገተው ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር በመሆን ባዉቺ የተባለውን ግዛት አገረ-ገዥ በሚያነጋግሩበት ወቅት መሆኑን አዘጋጁ ተናግሯል።

ፖሊስ በበኩሉ ግን ሳሊሱን የያዝኩት አገረ-ገዢውን በመቃወም ላይ የነበሩ ሰዎችን በሚያነጋግርበት ወቅት ደጋፊዎቻቸው ስላጠቁት ለደህንነቱ ስል ነው ብሏል።

ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ቡድኖች እና የጸጥታ ኃይሎች 13 የሚሆኑ ሌሎች ጋዜጠኞችንና የሚዲያ ሰራተኞችን አስፈራርተዋል፣ አጥቅተዋል አልያም አግተዋል ሲል ሲፒጄ ቃለ መጠይቅ አደረኳቸው ካላቸው ወገኖችና ሪፖርተሮች የደረሰውን መረጃ አጋርቷል።

ሲፒጄ የፖሊስ ቃል አቀባይንና አገረ-ገዢውን አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቆ መልስ እንዳላገኘ አመልክቷል።

በናይጄሪያ ባለፈው ቅዳሜ ከተካሄደው ምርጫ ቀናት ቀደም ብሎ ጋዜጠኞች አንድም ተጠቅተዋል አልያም ምርጫውን እንዳይዘግቡ ተከልክለዋል ብሏል ሲፒጄ ባወጣው መግለጫ።

XS
SM
MD
LG