ጸሃፊና የንዋይ ካፒታሊስት የሆኑት ጄ.ዲ. ቫንስ በትረምፕ ይደግፉ የነበሩ እጩ ሲሆኑ፣ በኦሃዮ የሴኔቱን ወንበር ከዲሞክራቱ ቲም ራያን ነጥቀዋል።
በፔንሲልቬኒያ ግን ዲሞክራቱ ጃሽ ሻፒሮ በትረምፕ ሲደገፉ የነበሩትን ዳግ ማስትሪያኖን በአገረ ገዢነቱ ውድድር አሸንፈዋል።
በኒው አምሸር ዲሞክራቷ ሴናተር ማጊ ሃሰን በትረምፕ የታጀቡትን ዳን ቦልዶክ ዘርረዋል። ቦልዶክ ትናንት ማታ ሽንፈታቸውን አምነዋል።
ትኩረት ባገኘው የፔንሲልቬኒያ የሴኔት መቀመጫ ተቀራራቢ ውድድር፣ በትረምፕ ሲደገፉ የቆዩት ታዋቂ ዶ/ር መሃመት ኦዝ በዲሞክራቱ ጃን ፈተርማን ተሸንፈዋል።
ጆ ባይደንና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፈተርማንን ለማዳን ወደ ሥፍራው ተጉዘው የምርጫ ዘመቻ አድርገው ነበር።
በአሪዞና በም/ቤትም ሆነ በሰኔት ውድድሩ ዲሞክራቶቹ በትረምፕ ይደገፉ የነበሩትን እጩዎች በመምራት ላይ ናቸው። ቆጠራው ገና በመካሄድ ላይ ነው። በግዛቱ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ መቁጠሪያ ማሽኖቹ እክል ገጥሟቸዋል።
ከትረምፕ ጋር መልካም ግንኙነት የሌላቸው ሁለት ሪፐብሊካን ግን፣ በኒው ሃምሸር ክሪስ ሱኑኑ እና በጆርጂያ ብራያን ከምፕ አገረ ገዢነቱን ለማሸነፍ በቅተዋል።
ብራያን ከምፕ ከትረምፕ ጋር የተቃቃሩት ባለፈው ምርጫ ትረምፕ ጆርጂያን አሸንፊያለሁ ብለው በሃሰት መናገራቸውን በመቃወማቸው ነው።
በሚቺጋንና በጆርጂያ ዲሞክራቶቹ በትረምፕ ከሚደግፉ እጮዎች ጋር ለህግ መወሰኛ ም/ቤት መቀመጫና ለአገረ ገዢነት ያደረጉት ፉክክር ቆጠራ ገና አላለቀም።
ቆጠራው የፓርቲዎቹን የወደፊት ዕጣና የኮንግረስን ስሪት ይወስናል።