በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የብሪታኒያ እስር ቤቶች በሁከት ተሳታፊዎች ተጠለቅልቀዋል


በዩናይትድ ኪንግደም ዙሪያ ፀረ-ኢሚግሬሽን ተቃውሞዎች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም ዙሪያ ፀረ-ኢሚግሬሽን ተቃውሞዎች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል።

ብሪታንያ በዚህ ወር በነበረው ከፍተኛ ሁከት በወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ የተያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ሌላ ማቆያ ስፍራ እስክታዘጋጅ ድረስ በተጨናነቁት ፖሊስ ጣቢያዎች እንደምታቆያቸው አስታወቀች፡፡

የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር መንግሥት፣ ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ እስካሁን ከ1,100 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።

በቅርቡ ስደተኞች እና ሙስሊሞች ላይ ባነጣጠረው የዘረኝነት ጥቃት የተነሳውን ሁከት ተክትሎ የሚያዙት ሰዎች የእስር ቤቶች መጨናነቅ ቀውስ መፍጠራቸው ተገልጿል፡፡

የተፈጠረው የማረፊያ ቤቶች እጥረት ቀውስ ባለሥልጣናት “ተጨማሪ እስረኞችን ከወዲሁ እንለቃን” እንዲሉ እያስገዳደዳቸው መሆኑ በሮይተርስ ዘገባ ተጠቅሷል፡፡

መንግሥት አዲስ ሊወስደው ያሰበው ጊዜያዊ እርምጃ ተጠርጣሪዎች ወደ ፍርድ ቤት የሚጠሩት በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙት ከ100 በላይ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ እስረኞችን የሚያስተናግድ ክፍል መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ያ እስኪሆን ድረስ የታሰሩት ሰዎች “በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋል” ሲሉ ባለሥልጣናቱ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡

የእስር ቤቱ ሚኒስትር ጄምስ ቲምፕሰን በሰጡት መግለጫ “የፍትህ ስርዓቱን የተረከብነው በችግር ውስጥ ሆነን እና ለትልቅ ቀውስ ተጋልጠን ነው፡ በዚህም የተነሳ ሥራውን ለማስቀጠል አስቸጋሪ ግን አስፈላጊ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ተገድደናል።" ብለዋል፡፡

ባለፈው ወር ገና ሥልጣን የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር የተጨናነቁ እስር ቤቶችን ከወዲሁ ከገጠማቸው ቀውስ ጋር አብረው መውረሳቸው ከአስቸጋሪ አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል፡፡

ብሪታንያ በምዕራብ አውሮፓ ከፍተኛው የእስረኞች ቁጥር ያላት ሲሆን ይህም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡

በተለይ የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የተፈጠረው የፍርድ ቤቶችና ችሎቶች መዘግየት አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከባባድ ወንጀል ለፈጸሙት ፍርደኞች የሚሰጡት የረጃጅም ጊዜ የእስራት ዘመን መብዛትም የእስረኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አስተዋጾኦ አድርጓል፡፡

በብሪታኒያ ከባድ ወንጀለኞች ቢያንስ 65 በመቶ የሚሆነውን የእስር ጊዜያቸውን በወህኒ ቤት እንዲያሳልፉ ይጠበቃል፡፡

ይሁን እንጂ ባለፈው ወር ስታርመር ይፋ ባደረጉት እቅድ መሰረት፣ አብዛኛዎቹ እስረኞች 40 ከመቶ የእስር ጊዜያቸውን ካሳለፉ በኋላ ከእስር ሊለቀቁ እንደሚችሉ ተነገሯል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG