በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የታሠሩ “ጋዜጠኞች እንዲፈቱ” አርቲክል 19 ጠየቀ


ፎቶ ፋይል፦ በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ ለሽያጭ የተሰናዱ ጋዜጦችና መጽሔቶች
ፎቶ ፋይል፦ በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ ለሽያጭ የተሰናዱ ጋዜጦችና መጽሔቶች

ኢትዮጵያ ውስጥ የታሠሩ ጋዜጠኞችን መንግሥቱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ “አርቲክል 19” ጠይቋል። ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ “መገናኛ ብዙኃንን የማሸማቀቅ” ሲል የጠራው አድራጎትም እንዲቆም አሳስቧል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1941 ዓ.ም. በፀደቀውና ኢትዮጵያም የህጎቿ አካል ባደረገችው “የሰብዓዊ መብቶች ሁለንተናዊ ስምምነት” ላይ የሠፈረውንና “አመለካከትንና ሃሳብን ያለአንዳች ጣልቃገብነት በነፃነት የመያዝና የማስተላለፍ መብት”ን በያዘው “አንቀፅ 19” ስም የሚንቀሳቀሰው ቡድን ከትናንት በስተያ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ 16 ጋዜጠኞች መታሰራቸው እንደሚያሳስበው አስታውቋል።

‘ታስረዋል’ ያላቸውን አብዛኞቹን ጋዜጠኞችና የዩትዩብ ሚዲያ አዘጋጆች በስም የዘረዘረው አንቀፅ 19 “መንግሥት ጋዜጠኞቹን በአስቸኳይ መልቀቅና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ሙሉ በሙሉ መጠበቅ ማረጋገጥ አለበት” ብሏል። የድርጅቱ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ሙጋምቢ ኪአዪ “መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ግጭቶችን ሚዲያውን ለማሸማቀቅ ጉዳይ መጠቀም የለበትም” ማለታቸውንም መግለጫው አመልክቷል።

መግለጫው አክሎም “የሰሞኑ እሥራት በመገናኛ ብዙኃን ላይ እየተፈፀመ ያለ ማስፈራትና ወከባ አካል ነው” ብሏል።

የሚዲያ ባለሙያዎችን መታሠር “ሕገወጥ” ሲል የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም “ሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ” ሲል ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

አሁን 18 ጋዜጠኞች ታስረው እንደሚገኙ የገለፁት የኮሚሽኑ የሕግና የፖሊሲ ዳይሬክተር ታሪኳ ጌታቸው ሁኔታው “ከሚዲያ ሕጉ ጋር የሚፃረር መሆኑ ኮሚሽኑን ያሳስበዋል” ብለዋል።

ሰሞኑን ፍርድ ቤት የቀረቡ ጋዜጠኞች እና ሌሎች የሚዲያ ሠራተኞች ጉዳያቸው በሚዲያ ሕጉ መሠረት እንዲታይ መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበርም ይህንኑ ሀሳብ እንደሚጋራ ፕሬዚዳንቱ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ገልጿል። የሚዲያ ባለሙያዎቹ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው መከታተል እንዳለባቸው ጥበቡ አሳስቧል።

ሰው የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎችን እየተጠቀመ ሃሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብቱን ተግባራዊ ማድረጉ በብዛት እየተስተዋለ መሆኑን የጠቆመው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በአንፃሩ በሚዲያ ስም የፖለቲካ አጀንዳ የሚያስተጋቡ መኖራቸው ከዘርፉ ተግዳሮት እንዱ መሆኑን አመልክቷል።

ሆኖም ችግሮች በሚዲያ ሕግና በሚድያው ምክር ቤት መታየት እንዳለባቸው የገለፀው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዚዳንት ማኅበሩ የታሠሩ ጋዜጠኞችን ጉዳይ እየተከታተለ መግለጫ እያወጣ መሆኑን፣ ሁኔታውንና አቋሙንም ለመንግሥትና ለሌሎችም አካላት በደብዳቤ ማሳወቁን ተናግሯል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታሠሩትን ጋዜጠኞች እየጎበኘና ጉዳያቸውንም በቅርብ እየተከታተለ እንደሚገኝ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም እየተነጋገሩ መሆኑን የኮሚሽኑ የሕግና ፖሊሲ ዳይሬክተር ታሪኳ ጌታቸው ገልፀውልናል።

ዩናይትድ ስቴትስና ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ)ም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጋዜጠኞችና ሌሎች የሚዲያ ሠራተኞች መታሰር እንደሚያሳስባቸው መግለፃቸው ቀደም ሲል ተዘግቧል።

የመንግሥትን ሃሳብና ምላሽ የያዘ ማብራሪያ ለማግኘት ዛሬም ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፐሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ለመንግሥቱ መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ሣምንት በሰጡት ማብራሪያ የሚዲያ ባለሙያዎቹ መታሰር “ሕግን የማስከበር እርምጃው አካል ነው” ብለው ነበር።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎትም ከሁለት ሣምንታት በፊት ባወጣው መግለጫ “አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ውስጥ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱት ነው” ያለው “ሕግ የማስከበር እርምጃ ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት በወሰነው መሠረት የተፈፀመ እንደሆነ አመልክቶ “ነፃነትንና መብትን ከለላ በማድረግ የሚፈፀም የትኛውንም ዓይነት እኩይ ተግባር መንግሥት አይታገስም” ብሏል።

XS
SM
MD
LG