በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ


«የሳይንስ አካዳሚው ነጻና በብቃት ላይ የተመሰረተ አካዳሚ እንዲሆን ከመንግስት ወገን ፍላጎት አለ፤» ተባለ።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዛሬ የመጀመሪያዉን ጉባኤ ሲከፍት ዋና ርእሱን «ሳይንስና ቴክኖሎጂ የአገር ህልዉና መሰረት፤» ብሎታል። የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ደምሴ ሃብቴ በመክፈቻ ንግግራቸዉ፥ አካዳሚዉ የሳይንስ ትምህርት ምርምርና እዉቀት ተስፋፍቶ ሳይንሳዊ ባህልም በኢትዮጵያ ዉስጥ ጎልብቶ ማየት ራእዮ መሆኑን ገልጸዋል።

የሳይንሳዊ እዉቀትና ግኝት የመጨረሻዉ ግብም የህዝብን ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ህይወት መለወጥ የአካዳሚዉ እምነት እንደሆነም ዶክተር ደምሴ ሃብቴ አስረድተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዜናዊን መልክት ለጉባኤዉ በንባብ ያሰሙት፥ በሚኒስትር ማእረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ፥ «አካዳሚዉ ከእዉቀት ጀንበር ወይንም ከጠንካራ የፈጠራ ተግባር እንዳንርቅና እንዳንባዝን በማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ህዳሴ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል፤ መንግስትም አካዳሚዉ በበኩሉ በተልእኮዉ ዉጤታማ እንዲሆንና የተቻለዉን ሁሉ ያደርጋል፤» ብለዋል።

በጉባኤው መክፈቻ ንግግር ካሰሙ ተናጋሪዎች አንዱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዲኤታው አቶ መሃሙድ ሃሰን ጋዝ፣ አካዳሚዉ በፓርላማ በሚወጣ ህግ እዉቅና አግኝቶ ነጻና ብቃትን መሰረቱ ያደረገ፣ ለመንግስት አካላት አድሎ የሌለዉ፤ እንዲሁም በማስረጃ ላይ የተመሰረተና የሚታመን ምክር ሰጪ ይሆናል ብለዋል።

በጉባኤዉ ከተገኙት አያሌ እዉቅ ምሁራን መካከል እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር የ2009 የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሸላሚና የፐርዱ ዩኒቨርሲቲ አግሮኖሚስቱ ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ በበኩላቸው፥ «ሳይንቲስቶች በሳይንሳዊ ጉዳዮች ላይ በነጻነትና ያለ ፖለቲካ አድሎ መንግስትን መምከር ሲችሉና መንግስትም ምክራቸዉን በማክበር ሲቀበል መላ ማህበረሰብ ተጠቃሚ ይሆናል፤» ብለዋል። የመለስካቸዉ አመሃን ዘገባ ያዳምጡ።

XS
SM
MD
LG