በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቦቢ ዋይን ታሰረ


በዩጋንዳ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ቦቢ ዋይን
በዩጋንዳ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ቦቢ ዋይን

በዩጋንዳ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ የሆነው ቦቢ ዋይን በምርጫ ዘመቻ ላይ እንዳለ በዚህ ሳምንት ለእስር ተዳርጓል። የዋይን የአሁኑ እስር ፕሬዝዳንት ያዌሪ ሙሴቬኒን ከስልጣን ለማውረድ የምርጫ ፉክክሩን ከጀመረ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ከዋይን እስር ቀደም ብሎ መንግሥት በዋይን ደጋፊዎች ላይ ያደሰውን የመብት ጥሰት ሲመዘግብ የነበረው የሰብዓዊ መብት ጠበቃ በዋስትና ከእስር ተለቋል።

ከሙዚቃ አቀንቃኝነት ወደ ፖለቲካው የተቀላቀለው ቦቢ ዋይን ካላንጋላ በተሰኘው የዩጋንዳ ከተማ ውስጥ የምርጫ ዘመቻ እያደረገ ባለበት ወቅት ነው ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለው። የዋይን ብሄራዊ አንድነት መድረክ ፓርቲ ቃል አቀባይ ጁዌል ሴንዮኚ ስለሁኔታው ሲገልፁ እንዲህ ይላሉ።

"ካላንጋላ የምርጫ ዘመቻ እንዳይካሄድባቸው ከተከለከሉ ከተሞች አንዱ ባለመሆኑ ወደ እዛ ሄዷል። ግን በሚያስደነግጥ ሁኔታ እዛ ከደረሰ በኃላ ወታደሮች ከበውት እሱንና 90 የሚሆኑ ጠቅላላ የቡድኑን አባላት አስረው ወደ ተለያየ ቦታ ወሰዷቸው። እሱ በሂሊኮፕተር ነው የተወሰደው፣ ግን የት እንደሆነ አላቅንም።"

ሴንዮኚ ጨምረው የሙሴቨኒ መንግስት እያደረገ ያለው፣ የብሄራዊ አንድነት መድረክ ፓርቲውን ማስፈራራት ነው ይላሉ። "ይሄ ሁሉ መንግስት የሚያካሂደው ህገወጥ ተግባር እኛን ለማስፈራራት እና ከአላማችን ለማሰናከል ነው። እኛ ጋን ከበፊቱ የበለጠ ቆርጠን ተነስተናል። የበለጠ ጫና እናሳድራለን፣ ወደፊትም እንሄዳለን። ሙሴቬኒ ከስልጣን መውረድ አለበት።

የዩጋንዳ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ የብሄራዊ አንድነት መድረክ ፓርቲ ስለቦቢ ዋይን መታሰር የሰጠውን መረጃ ውሸት ነው ሲል ህብረተሰቡ እንዳያዳምጥ ጠይቋል።

ፖሊስ ዋይን የታሰረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ባለበት ወቅት የምርጫ ኮሚሽኑ እና የጤና ሚኒስቴር ያወጧቸውን መመሪያዎች ቸል በማለት በተደጋጋሚ ትላልቅ ሰልፎችን በማካሄዱ ነው ብሏል። ዋይን መኖሪያው ወደ ሆነው ካምፓላ መወሰዱንም ግልጿል።

ፓሊስ ጨምሮ የዋይን ምርጫ ዘመቻ ቡድን አባላት አብረው የታሰሩት በካሜራ በተቀረፀ ማስረጃ የፖሊስ መኪና ጎማ ሲያተነፍሱ፣ አመፅ ሲያስነሱ፣ የፖሊስን ስራ ሲያውኩ እና ለኮሮና ቫይረሰ የወጡትን የጤና እና የደህንነት መመሪያውች ሲጥሱ በመገኘታቸው ነው ብሏል።

ከዋይን እስር ቀደም ብሎ የሰብዓዊ መብት ጠበቃው ኒኮላስ ኦፒዮ ከዘጠኝ ቀናት እስር በኃላ በዋስ ተለቋል። ባለስልጣናት ኦፒዮን የከሰሱት በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ሲሆን ተቺዎች ግን ኦፒዮ የታሰረው የተቃዋሚ ደጋፊ በመሆኑ ነው ይላሉ።

ኦፒዮ ዋስትናው የተፈቀደበትን የፍርድ ቤት ሂደት የተከታተለው ካታሊያ ከተሰኘው የመንግስት እስር ቤት ሆኖ በቪዲዮ አማካኝነት ነው። አቃቤ ህጉ ኦፒዮ የተከሰሰበት ጉዳይ 15 አመታት የሚያስፈርድ ጠንካራ ክስ መሆኑን በመግለፅ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዳይሰጠው ጠይቆ ነበር። ነገር ግን ዳኛው ጄን ካጁጋ ጥያቄውን አልተቀበሉትም።

"ዋስትናውን ከመከልከል ይልቅ ወደመፍቀዱ አዘነብላለሁ። ዋስትናውን በመፍቀድ ፍትህ እንዲገኝ ማድረግ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ነው የሚሆነው።"

ቻፕተር ፎር የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ድርጅት እንዳስታወቀው ኦፒዮ በታሰረበት ወቅት ባለፈው ወር በተካሄደው የሁለት ቀን ተቃውሞ ሰልፍ ወቅት በተፈፀሙ ግድያዎችና እስሮች ዙሪያ መረጃዎች እያሰባሰበ ነበር።

በህዳር ወር አጋማሽ ላይ የዋይንን እስር ተከትሎ በተቃዋሚ ደጋፊዎችና በፀጥታ አስከባሪ አባላት መካከል በተነሳ ግጭት 56 ሰዎች መገድላቸው ይታወሳል። ተቺዎችም የዩጋንዳ መንግስትንበተለይ በምርጫው ዙሪያ የሚቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችንና አመራሮችን ኢላማ አርጎ እያጠቃ እንደሆነ ይናገራሉ።

በዩጋንዳ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እአአ በያዝነው ዓመት በጥር 14 ይካሄዳል።

XS
SM
MD
LG