በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሱዳን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካርቱም የላካቸው የጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ ናቸው አለች


የሱዳን የሃገር ውስጥ የዜና ወኪል የሆነው ሱና እሁድ ዕለት ባወጣው ዘገባ፤ ቅዳሜ ዕለት በመንገደኞች መጓጓዣ አይሮፕላን አማካኝነት ከአዲስ አበባ ካርቱም የገቡ የጦር መሳሪያዎች እንዳሉ እና የዛኑ ዕለት ማምሻውን በሱዳን መንግስት መወረሳቸውንም አስታውቋል፡፡ ሱና ባለስልጣናቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከአዲስ አበባ የገባውን የጦር መሳሪያ በተመለከተ ጥቆማ እንደደረሳቸው እና መሳሪያውም ወዲያው በጉሙሩክ መወረሱን ዘግቧል፡፡ አያይዞም ባለስልጣናቱን ጠቅሶ መሳሪያዎቹ እ.ኤ.አ በግንቦት 2019 ዓ.ም ከሩሲያ ወደ አዲስ አበባ ገብተው ለሁለት ዓመት ያህል መቆየታቸውንም ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም የዜና ወኪሉ “በአዲስ አበባ ያሉ ባለስልጣናት ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የጦር መሳሪያው በመንገደኛ መጓጓዣ አማካኝነት እንዲገባ ፈቅደዋል” በማለት ዘግቧል፡፡

ይህን ተከትሎ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል ሁኔታውን ለማጣረት ባደረገው ጥረት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የጽሁፍ ምላሽ ያገኘ ሲሆን በጽሁፍ መልዕቱም ላይ “በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት ወደ ሱዳን የተላኩት የጦር መሳሪያዎች የአደን መሳሪያዎች ሲሆኑ የመጓጓዣና የተቀባይ ሰነድ ያላቸው ናቸው” ያለ ሲሆን “የአደን መሳሪያዎቹ አዲስ አበባ ላይ በደህንነት ባለስልጣናት ማጣሪያ እየተደረገባቸው ለረዥም ጊዜ መቆየታቸውን ተከትሎ ተቀባዩ አካል አየር መንገዱን በሱዳን ፍ/ቤት መክሰሱን እና መሳሪያዎቹ ካልተላኩለትም 250 ሺ ዶላር ካሳ እንዲከፈለው መጠየቁን” የገለጸ ሲሆን "ከባለስልጣናቱ ይለፍ እንዳገኘን በሱዳን ወደሚገኘው ተቀባይ መሳሪያውን ልከነዋል" ሲል አስታውቋል፡፡

የሰነዶቹ እና የመሳሪያዎቹን መጓጓዝ ሕጋዊነት የሚያረጋግጥ ደብዳቤም ከሱዳን ውጪ ጉዳይ ሚኒስተር አለኝ ያለ ሲሆን በትዊተር ገጹ ላይም መሳሪያዎቹ የአደን መሆናቸውን እና ተቀባዩን የሚያመላክቱ ናቸው ያላቸውን ሰነዶችም በአባሪነት አያይዟል፡፡

በሌላ በኩል አሁን ማምሻውን የሱዳን የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር ለሮይተርስ በሰጠው መረጃ የጦር መሳሪያዎቹን ሕጋዊነት ማረጋገጡን ገልጿል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በ70 ሳጥን የገባው 270 የአደን ጦር መሳሪያ ሕጋዊ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ፍቃድ ያለው ዋኤል ሻምስ ኤልዲን የተሰኘው ተቋም ንብረት መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

ሱዳን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካርቱም የላካቸው የጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ ናቸው አለች
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:22 0:00



XS
SM
MD
LG