በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአርጀንቲናው ጎርፍ የሞቱት ሰዎች 16 ሲደርስ ሁለት ሕጻናት የደረሱበት ጠፍቷል


Aftermath of floodings in Bahia Blanca
Aftermath of floodings in Bahia Blanca

ባሂያ ብላንካ በምትባለው የአርጀንቲና የወደብ ከተማ በደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ የሞቱት ሰዎች ቁጥር አሻቅቦ 16 መድረሱን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ጥልቅ ውሃ ዋናተኞች ጎርፉ የወሰዳቸውን ሁለት ሕጻናት ፍለጋ ላይ ተሰማርተዋል፡፡

ከቦይኖ ሳይረስ ክፍለ ግዛት በስተደቡብ የምትገኘው ከተማ ከሀገሪቱ ትላልቅ ወደቦች አንዱ የሚገኝባት ስትኾን በዓመት የሚጥለው መጠን ያለው ዝናብ ዓርብ ዕለት በጥቂት ሰዓት ውስጥ ወርዶባታል። መንገዶች እንዲሁም በርካታ መንደሮች በአንድ ጊዜ በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል፡፡

በጎርፉ 400 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያለው መሠረተ ልማት እንደወደመ የከተማዋ ከንቲባ ፌዴሬኮ ሱስቤልየስ ተናግረዋል። 16 ሰዎች መሞታቸው እንደተረጋገጠ የገለጹት ከንቲባው ቁጥሩ ይጨምራል የሚል ስጋት መኖሩንም አክለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአንድ ዓመት እና የአምስት ዓመት ህጻናት የሆኑ እህትማማቾች በጎርፉ መወሰዳቸው መላ ሐገሪቱን አሳዝኗል፡፡ ሁለቱ ልጆች ከእናታቸው ጋር "ቫን" መኪና ጣሪያ ላይ ወጥተው እንደነበረ እና ጎርፉ ደርሶ ይዟቸው እንደሄደ የከተማዋ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡ ዋናተኞች አሁንም በአንድ ሜትር ከፍታ አካባቢውን ባጥለቀለው ውሃ ውስጥ ፍለጋ ቀጥለዋል፡፡

የአርጀንቲና መንግሥት በጎርፉ ለተጎዱት አካባቢዎች አስቸኳይ ጥገና ሥራ የሚውል 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ ተገልጿል፡፡

ባሂያ ብላንካ ከተማ ከአሁን ቀደምም ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ አደጋ ያጋጠማት ሲሆን እ አ አ በ2023 የጣለው ኃይለኛ ዝናብ 13 ሰዎች ሲገድል መጠነ ሰፊ የመሠረተ ልማት አውታሮች አውድሟል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG