በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አረና ሶስት የማእከላዊ ኮሚቴ አባላቱን አገደ


“የፓርቲውን ስም ለማጥፋትና ለማጉደፍ እንቅስቃሴ አድርገዋል፣” አቶ ገብሩ አስራት

የአረና ትግራይ ማእከላዊ ኮሚቴ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ባደረገው ስብሰባ በድርጅቱ ውስጥ ባጋጠመው ችግር ላይ ውይይት አካሂዷል። የድርጅቱን ህገ ደንብ በመጣስ ድርጅቱን በሚበታትን ተግባር ላይ ተሰማርተዋል ያላቸውንም ሶስት አባላት ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲታገዱ ውሳኔ አሳልፏል።

ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ አቶ ገብሩ አስራት በቡድን መደራጀትን የማይፈቅደው የድርጅታቸው ህገ ደንብን ባለማክበራቸው ሶስቱ አባላት በድርጅቱ ውስጥ ያላቸውን አባልነት ሊያጡ እንደቻሉ ገልፀዋል። በቡድን ተደራጅተው የነበሩት አባላትም “የፓርቲው አቋም ያልሆኑ ጉዳዮችን እንደልዩነት በማቅረብ የፓርቲውን ስም ለማጥፋትና ለማጉደፍ እንዲያዉም የተከፋፈለና የተበታተነ አስመስሎ ለማቅረብ እንቅስቃሴ አድርገዋል፣” ሲሉም አቶ ገብሩ አስራት አብራርተዋል።

በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች እንቅስቃሴያቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ሲገልፁ እንደቆዩና ወደ ምርጫ ቦርድ ሄደውም አዲስ ፓርቲ ለመመስረት እቅድ እንደነበራቸውና ለዚህም ምክር ጠይቀው እንደነበር የተናገሩት አቶ ገብሩ ይህን የመሳሰሉ ድርጊቶችን በማየቱ ድርጅቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የተገደደ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሰዎቹ ተፀፅተው አቋማቸውን ካስተካከሉ ግን ድርጅቱ በድጋሜ እድል ሊሰጣቸው ዝግጁ መሆኑን አክለው ገልፅዋል።

በመጨረሻም ዘንድሮ የተካሄደው ምርጫን አስመልክቶ አቶ ገብሩ አስራት አረና ትግራይ ያገኘው ድምፅ የሚበረታታ እንደሆነ ጠቅሰው ድርጅቱን ለመረጠው ህዝብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የታገዱት አባላት ለግዜው መግለጫ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

XS
SM
MD
LG