በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካው የቪዛ እገዳ እና የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን

ዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከትግራዩ ቀውስ ጋር በተያይዘ በአሁኖቹና በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣንት እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎችና የህወሓት አባላት ላይ የቪዛ ማዕቀብ መጣሉን፣ ትናንት እሁድ የወጣው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አመልከቷል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የቪዛ ገደቦችና ተያያዥ ውሳኔዎቹ የሁለቱን አገራት የቆየ ወዳጅነት የሚሸርሸር መሆኑን ገልጾ፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት መልሳ እንድትፈሽ ያስገድዳታል ብሏል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን ትናንት በሰጡት መግለጫ፣

“በትግራይ ውስጥ ያለው ቀውስ እንዲፈጠርም ሆነ እንዲወሳሰብ በማድረግ ተጠያቂ በሆኑ ግለሰቦች፣ በአሁኖቹና በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ወታደራዊ የደኅንነት አባላት፣ እንዲሁም ለአማራ ክልል ኃይሎችና መደበኛና መደበኛ ላልሆኑ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ/ህወሓት/ አባላት፣ ፣ የቪዛ ማዕቀብ እንዲደረግ የተወሰነ መሆኑን አስታውቃለሁ" ብለዋል፡፡

"ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ባለው ቀውስና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛትና ብሄራዊ አንድነት፣ አደጋ በሆኑ ሌሎች ችግሮች ጥልቅ ስጋት አላት” ያሉት ብሊንከን፣ ትግራይ ውስጥ ያሉ ሰዎች በመካሂድ ላይ ባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጥቃትና በደሎች እየተሰቃዩ ነው፡፡ በአስቸኳይ የሚያስፈልጉ የሰብአዊ እርዳታዎች በኢትዮጵያና በኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም በሌሎች ታጣቂ ኃይሎች እንዲታገዱ ተደርገዋል" ብለዋል፡፡

ብሊንከን "ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ቢደረጉም፣ በትግራዩ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ግን ግጭቱን ለማቆምም ሆነ ፖለቲካዊ ቀውሱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰዱት፣ ይህ ነው የሚባል ምንም ዓይነት እርምጃ" አለመወሰዱንም ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ “ዩናይትድ ስቴትስ ግድያዎችን፣ ማፈናቀሎችን፣ ስር የሰደዱ የጾታ ጥቃቶችንና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰትና በደሎችን እጅግ አጥብቃ ታወግዛለች፡፡ ትግራይ ውስጥ የውሃ ምንጮች፣ ሆስፒታሎች እና የህክምና ተቋማትን ጨምሮ በወደሙት የሰላማዊ ዜጎችና ንብረቶችም እኩል አሳዝነውናል፡፡” በማለት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብአዊ መብቱ ጥሰቶችና ጥቃቶቹ ተሳታፊ የሆኑትን ሁሉ ተጠያቂ በማድረግ፣ የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት በመጠበቅም ሆነ የሰብአዊ እርዳታው ተደራሽነት እንዲኖር በማድረግ ህዝባዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የጠየቁት ብሊንከን “ኤርትራ መንግሥት በይፋ የገባውን ቃል ጠብቆ ወታደሮቹን ዓለም ወደሚያወቀው የኤርትራ ግዛት ክልል እንዲመልሳቸው እንጠይቃለን” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በክልሉ የሚካሄደው ግጭትና ጠብ አጫሪነቱ በአስቸኳይ ካልቆመ፣ የሚያስፈልገውን አጣዳፊ የሰአብዊ እርዳታ በስፋት ማዳረስ ስለማይቻል አሁን የሚታየው የምግብ እጥረት ወደ ረሀብ አደጋ ሊያመራ ይችላል” በማለትም በአካባቢው ተደቅኗል ስላሉት አደጋ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

“በትግራይ ለተፈጠረው ቀውስ በመፍትሄነት የቀረቡ አማራጮችን ሁሉ ያልተቀበሉ ወገኖች፣ ከዩናትድ ስቴትስም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ሌሎች ተጨማሪ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ ማወቅ ይኖርባቸዋል” ያሉት ብሊንከን “ሌሎች መንግሥታትም ይህንን እርምጃችንን እንዲደግፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን፣ የቪዛው ማዕቀብ በኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ባለው ህዝብ ላይ በተፈጸመው ያልተገባ ጥቃት የተሳተፉ ወይም በደል የፈጸሙ፣ በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንዳይደርስ ያደናቀፉትንም ሁሉ የሚመለከት መሆኑን ገልጸው እቀባው በዚህ ድርጊት የተሳተፈውን ሰው የቅርብ ቤተሰቦችንም ሊጨምር ይችላል በማለት አስረድተዋል፡፡

ከባለሥልጣንቱና ግለሰቦቹ በተጨማሪ በአገሪቱ ላይም ስለሚጣለው ተጨማሪ ማዕቀብ ብሊንክን ሲገልጹ “ከዚህ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ በሚሰጡ የኢኮኖሚና የደኅንነት ነክ እርዳታዎች ላይ መጠነ ሰፊ የሆኑ ገደቦች የጣልን ሲሆን፣ በመከላከያው ዘርፍ ያለንን የንግድ ቁጥጥርና ፖሊሲያችንንም ከዚህ ጋር እንዲስማማ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም “የምንሰጠውን የሰአብአዊ እርዳታ የምንቀጥልበት ሲሆን፣ በተወሰነ ደረጃም እንደ ጤና፣ የምግብ ዋስትና፣ ለሴቶችና ልጃገረዶች እገዛ፣ ለሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲ፣ ለመልካም አስተዳደርና ግጭትን ቅነሳ ባመሳሰሉት ዘርፎች የምንሰጠውን እርዳታ እንቀጥልበታለን” ብለዋል፡፡

ኤርትራን በሚመለከትም “ዩናይትድ ስቴትስ ለኤርትራ እንዳይሰጡ የወሰነቻቸውን መጠነ ሰፊ የእርዳታ ማዕቀበኞችን አሁንም ትቀጥልበታለች”በማለት ያለውን አቋም ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም “ዩናይትድ ስቴትስ ቀውሱ ዘላቂ የሆነ የፖለቲካ መፍትሄ እንዲያገኝ አሁንም ጥሪዋን ታቀርባለች፡፡” ያሉት ብሊንከን “እኛ በትግራይ የተፈጠረውን ቀውስ እንዲወገድ ፣ ኢትዮጵያውያን እርቅና ውይይት አድርገው አሁን የገጠማቸውን መከፋፈል እንዲያስወግዱ ለመርዳት ቁርጠኝነታችንን እንገልጻለን” በማለት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መግለጫ

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ፣ የቪዛ ገደቦችና ተያያዥ ውሳኔዎቹ የሁለቱን አገራት የቆየ ወዳጅነት የሚጎዳ መሆኑን ገልጾ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት መልሳ እንድትፈሽ ያስገድዳታል ብሏል፡፡

ይህ ውሳኔ የመጣው የኢትዮጵያ መንግሥት ከዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ጋር ሁለቱን አገራት በሚያሳስቧቸው የጋራ ችግሮች ላይ ገንቢ የሆነ ውይይት በማድረግ ላይ በሚገኙበት ጊዜ ነው ያለው መግለጫ

“ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በቅርቡ የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክትኛ ተደርገው ከመጡት ጄፍሪ ፌልትማን ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ምክክር ማካሄዳቸውም ይህንን መሰረት በማድረግ መሆኑን” አመልክቷል፡፡

“ኢትዮጵያ አዲስ ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀች በምትገኝበት በዚህ ወቅት ይህ ውሳኔ መውጣቱ የሚያስተላልፈው መጥፎ መልዕክት” እንዳለም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ አስታውቋል፡፡

አያይዞም “ኢትዮጵያ በዚህ የምርጫ ወቅት ከአሜሪካ የምትጠብቀው ድጋፍና መረዳትን እንጂ ምርጫው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳርፈውን እንዲህ ያለውን ውሳኔ አልነበረም” ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ምኒስቴሩ መግለጫ የአሜሪካ መንግስት ከሁለት ሳምንት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር የኢትዮጵያን መንግሥት በእኩል ደረጃ ማስተናገዱ እግጅ በጣም የሚያሳዝን መሆኑን ገልጾ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር ተቀምጦ ድርድር እንዲያደርግ ማስገደድ እንደማይቻልና ቡድኑ እንዲያንሰራራ የሚደረገውን ማንኛውንም አይነት ሙከራ ውጤታማ እንደማይሆን መንግሥትም እንደማይፈቅደው” አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ብሄራዊ ውይይት እንዲኖር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየሰራ መሆኑን መግለጫው አመልከቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በተከታታይና በግልጽ እንዳስታወቀው፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት፣ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጾ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን እንዴት አድርጋ መምራት እንደሚገባ ማንም ሊነግራት አይገባም ብሏል፡፡

በትግራይ የሰአብዊ መብት ጥሰት የፈጸሙትንም ተጠያቂ ለማድረግ የገባውን ቃል መንግሥት የሚያሟላ መሆኑን አመልከቶ በክልሉ የሰአብ ዊ እርዳታ ከሚሰጡ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰ ጋር አብሮ ለመስራት ያልተቋረጠ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በሌላም በኩል የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ትላንት ይፋ ስላደረጉት፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለሥልጣኖች ላይ የቪዛ ማዕቀብ ለመጣል ስላወጡት መግለጫቸው፣ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን አምባሳደር ፍሰሀ አስገዶምን ጋብዘናል።

ዝርዝሩን ከተያይዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

የአሜሪካው የቪዛ እገዳ እና የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ
please wait

No media source currently available

0:00 0:10:47 0:00


XS
SM
MD
LG