የነዳጅ ላኪ አገራት ድርጅት (ኦፔክ)፣ በመጪው ዓመት የምርት ኮታን ለመቀነስ መወሰኑን ተከትሎ፣ አንጎላ ድርጅቱን ለቃ እንደምትወጣ አስታውቃለች፡፡
ውሳኔው ላይ በቀላሉ አለመደረሱን ያወሱት የማዕድን እና ፔትሮሊየም ሚኒስትሩ ዲያማንቲኖ አዜቬዶ፣ የኦፔክ አባል መሆናቸው አገራቸውን እየጠቀመ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ኦፔክ የአንጎላን ጥቅም እያስጠበቀ ባለመሆኑ ለመልቀቅ መወሰኑን ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።
በፕሬዝደንት ጆአ ሎሬንሶ የተመራው የአገሪቱ መንግስት ካቢኔ፣ መዲማዋ ሉዋንዳ ላይ ባደረገው ስብሰባ ውሳኔው ላይ መድረሱ ታውቋል።
የነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ ለማድረግ፣ ኦፔክ ባለፈው ወር ምርትን ለመቀነስ በመወሰኑ፣ አንጎላ ደስተኛ እንዳልሆነች ሚኒስትሩ ለአገሪቱ ብሔራዊ ቴሊቪዥን ተናግረዋል።
ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ውስጥ አንጎላ እና ናይጄሪያ ትልቅ የነዳጅ አቅራቢዎች ሲሆኑ፣ ባለፈው ወር ኦፔክ የምርት ኮታ እንዲቀንስ ማድረጉ፣ የሚያገኙትን የውጪ ምንዛሪ እንዲቀንስ ያደርጋል በሚል ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር።
መድረክ / ፎረም