በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አርቲስት አንዱዓለም ጎሣ ተጨማሪ 13 ቀናትን በእስር እንዲቆይ ፍርድ ቤት ፈቀደ


አርቲስት አንዱዓለም ጎሣ ተጨማሪ 13 ቀናትን በእስር እንዲቆይ ፍርድ ቤት ፈቀደ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:00 0:00

አርቲስት አንዱዓለም ጎሣ ተጨማሪ 13 ቀናትን በእስር እንዲቆይ ፍርድ ቤት ፈቀደ

ባለፈው ሰኞ ሌሊት፣ ከምትኖርበት ሕንፃ አምስተኛ ፎቅ ላይ ቁልቁል ወድቃ ሕይወቷ ካለፈው፣ ሞዴል እና የማስታወቂያ ባለሞያ ቀነኒ አዱኛ ሞት ጋራ በተያያዘ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የሚገኘው እጮኛዋ አርቲስት አንዱዓለም ጎሣ፣ ተጨማሪ 13 ቀናትን በእስር ቆይቶ ምርመራ እንዲቀጥል ፍርድ ቤት አዘዘ።

የዐዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከቀነኒ ሞት ጋራ በዋና ወንጀል አድራጊነት የጠረጠረው አንዱዓለምን እንደኾነ በመግለጽ፣ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ የነበረ ሲኾን፣ ከጠበቃው ጋራ ፍርድ ቤት የቀረበው አንዱዓለም ደግሞ፣ የቀነኒ ሕይወት ያለፈው በአደጋ እንደኾነ በመግለጽ ከእስር እንዲፈታ አመልክቶ ነበር።

ሟች ቀነኒ አዱኛ ዋቆ፣ ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ፣ አምስተኛ ወለል ላይ ከሚገኘው የቤቷ የማብሰያ ክፍል ቨረንዳ በኩል፣ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ኹኔታ ቁልቁል ወደ ምድር ወድቃ ለሕክምና ርዳታ ወደ ያኔት ሆስፒታል እየተወሰደች ባለችበት ወቅት ሕይወቷ ማለፉን፣ የዐዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትላንት አስታውቆ ነበር።

የምርመራ መዝገቡን ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ፖሊስ፣ ሞዴል ቀነኒ፥ ሕይወቷ ባለፈበት ወቅት፣ ፍቅረኛዋ አርቲስት አንዱዓለም በቤት ውስጥ እንደነበር ጠቅሶ፣ የአስከሬን ምርመራ ውጤትን ጨምሮ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ለማቅረብ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ነበር።

"ለምርመራ የሚያበቃ በቂ ምክንያት የለም፤" በሚል ተቃውሞ ማቅረባቸውን ለአሜሪካ ድምፅ የገለጹት፣ የአርቲስት አንዱዓለም ጎሣ ጠበቃ አቶ ሊባን አብዲ ሑሴን፣ የቀነኒ ሕይወት ያለፈው "በአደጋ ነው" የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አስረድተዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፣ የአስከሬን ምርመራ ውጤትን ጨምሮ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አጠናቅሮ እንዲያቀርብ፣ ለፖሊስ ተጨማሪ የ13 ቀናትን የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ፣ ለመጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG