ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ በሚዛናዊነት እንዲመለከቱ ምሁራን አሳሰቡ፡፡ አሁን አሁን በድርጅቶቹ እየተስተዋሉ ነው ያሉት አድሏዊነት ችግሮችን ከማባበስ ያለፈ ኢትዮጵያን ከገባችበት ፈተና የሚታደጋት አይደለም ብለዋል ምሁራኑ፡፡
በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ አለሙ አራጌነ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ባልደረባው ደጀን የማነ ከአሜሪካ ድምጸ ራዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስረዱት ላለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አፋጣኝ ድጋፍና ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ሰብአዊ ቀውሶች ተፈጥረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ነን የሚሉተ አካላት ግን ለትግራይ ክልል በሰጡት ትኩረት ልክ ሌላውን ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያን ክልል አልተመለከቱትም ይላሉ፡፡
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳና ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣኑ ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤ ከውጭ አገራት መገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቆይታ ፍትሃዊ፣ ተፈጥሯዊ ድምበራችንን የማስመለስና፣ የሰብአዊ ርዳታ መተላለፊያዎች እንዲከፈቱ ጫና ለመፍጠር ሲሉ የገለጹትን ወታደራዊ ጥቃት መሰንዘራቸው ይታወሳል፡፡
እንደ አዲስ ባገረሸው ወታደራዊ ግጭት በቅርቡ ከራያ ቆቦ፣ ሰቆጣ አበርገሌና አፋር ፈንቲ ረሱ አካባቢዎች በመቶ ሽዎች የሚገመቱ ኗሪዎችና አርብቶ አደሮች ተፈናቅለው አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የአካባቢዎቹ አመራሮችም ሆኑ ተፈናቃዮች ለአሜሪከ ድምጽ ራዲዮ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።