ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ታስረው የሚገኙ በሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳይ እንደሚያሳስባቸውና እነ እስክንድር ነጋን የመሳሰሉ እሥረኞችም መለቀቅ አለባቸው ብለው እንደሚያምኑ የአውሮፓ ፓርላማ አባሏ አና ጎምሽ ለቪኦኤ ተናግረዋል።
አና ጎምሽ አክለውም “አስደናቂ” ሲሉ የጠሩት የኦሮሞና የአማራ መተባበር “ዴሞክራሲን በሃገሪቱ ውስጥ ለማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ ሁሉንም የጎሣ ቡድኖች ያሰባስባል፣ ያጠናክራል የሚል ተስፋ አለኝ” ብለዋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ለአውሮፓ ፓርላማ እማኝነት የሰጡበትን መድረክ ካዘጋጁትና ከጋባዦችም አንዷ የነበሩት የፓርላማው አባል አና ጎምሽ የኢትዮጵያ መንግሥት 528 እሥረኞችን በመፍታቱ የተፈጠረውን ደስታ ከተጋሩት ሰዎች አንዷ ቢሆኑም የኢትዮጵያን መንግሥት በብርቱ ኮንነዋል።
‘የፖለቲካ እሥረኞች ናቸው’ ብለው አና ጎምሽ የገለጿቸው በኢትዮጵያ እሥር ቤቶች ውስጥ በሺሆች ይገኛሉ ያሏቸው ሰዎች የተያዙትና የታሠሩትም “ለመብቶቻቸው በመነሣታቸው፣ ገዥውን ፓርቲ ለመውቀስ በመድፈራቸው፣ ጨካኝ፣ አምባገነንና ጨቋኝ የሆነውን ለአሥሮች ዓመታት የተጫነውን የሕወሐትና የኢሕአዴግ ሥርዓት ለመቃወም በመድፈራቸው ብቻ ነው” ብለዋል።
ምንም እንኳ የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃዎችና በዶ/ር መረራ ጉዲና መታሠር ላይ እጅግ የዘገየ ቢሆንም ተቃውሞውን የሚገልፅ መግለጫ ማውጣቱን ጎምሽ አስታውሰው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲህ ዓይነት መግለጫዎችን እርባና ቢስ እንደሆኑ በየወቅቱ ቢናገሩም መግለጫዎቹ “ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በእነዚህ ዓይነት ጭቆናዎች ላይ ያለውን ቁጣ የሚገልፁ፣ ለዴሞክራሲና ለፍትህ ለሚታገሉ ሁሉ ያለውን የአጋርነት ድጋፍ የሚያሳዩ ናቸው” ብለዋል።
ከእንደራሴ አና ጎምሽ ጋር በተደረገው ሙሉ ቃለ ምልልስ ላይ የተዘጋጀውን ዘገባ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ