በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቻድ የደህንነት መ/ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉ


ኒጃሜና፤ ቻድ
ኒጃሜና፤ ቻድ

በዋና ከተማዋ ኒጃሜና በሚገኘው የቻድ የሀገር ውስጥ ደህንነት ተቋም (ANSE) ዋና ጽህፈት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ መንግሥት ዛሬ ረቡዕ አስታወቀ።
ሌሊቱን ለተፈጸመው ጥቃት በያያ ዲሎ የሚመራውን ተቃዋሚውን ድንበር የለሽ ሶሻሊስት ፓርቲ (PSF) የፖለቲካ አንቂዎችን ተጠያቂ ያደረገው የቻድ መንግሥት “ሁኔታው አሁን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ሥር ሁኗል” ብሏል፡፡
“የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል ሌሎችም እየታደኑ ለፍርድ ይቀርባሉ” ሲልም የቻድ መንግሥት መግለጫ አክሎ ገልጿል፡፡
ጥቃቱ የደረሰው "በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ላይ የግድያ ሙከራ" በማድረግ የተጠረጠረ አንድ የፓርቲው አባል በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡
ዲሎ የአጎታቸው ልጅ የሆኑትን የቻድን የሽግግር ፕሬዝደንት ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖን አጥብቀው ይቃወማሉ፡፡
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ላይ ተፈጽሟል የተባለ ጥቃት “ሆን ተብሎ የተቀነባበረ” ነው ሲሉ ዲሎ አውግዘውታል።
በደህንነት ተቋሙ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ቻድ ማህማት ዴቢ ኢትኖ እና ዲሎ የሚወዳደሩበትን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እኤአ በግንቦት ወር እንደምታካሂድ በተገለጸ ማግሥት ነው፡፡
ማህማት ዴቢ ኢትኖ ሥልጣን የያዙት ቻድን ለሦስት አስርት ዓመታት የገዙት አባታቸው ኢድሪስ ዴቢ ኤትኖ እ አ አ በ2021 ዓም ከአማጽያን ጋር ሲዋጉ ከተገደሉ በኋላ ነው፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG