ፖሊስ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የጎማ ጥይቶችና ሌሎች ተተኳሽ መሣሪያዎችን መጠቀሙ በመላው ዓለም እየተለመደና እየጨመረ መጥቷል፤ ይህም ለብዙ የዓይን ጉዳትና አልፎ ተርፎም ለሞት እየዳረገ ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ጥናት አስጠንቅቋል፡፡
መሰረቱን በለንደን ያደረገው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ቡድን፣ ላላፉት 5 ዓመታት ከ30 በላይ አገሮች ላይ ጥናት ካደረገ በኋላ፣ የመግደል ኃይላቸው አነስተኛ መሆናቸው የሚነገርላቸውን እንዲህ ዓይነቶቹ የፖሊስ መሳሪያዎች አጠቃቀም ሆነ ሽያጭ ላይ የተሻለ ዓለም አቀፍ ቁጥጥር እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
አምነስቲ “አይኔ ፈንድቷል” (My Eye Exploded) በሚል ርዕስ ባወጣው አዲስ ሪፖርት “ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችና በአጋጣሚ በቦታው የተገኙ ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ በርካቶቹም በግድየለሽነት፣ ባልተመጣጠነና የመግደል ኃያላቸው አነስተኛ ናቸው በተባሉ የህግ አስከባሪ መሣሪያዎች ተገድለዋል” ብሏል፡፡
እነዚህ የጎማ ጥይቶችን ጨምሮ፣ አስለቃሽ ጭሶችና ተቃጣጣይ መሣሪያዎች፣ በደቡብ እና ማዕከላዊ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አፍሪካና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቀጥታ ወደ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ይተኮሳሉ ሲል አምነስቲ አመልክቷል፡፡
“ሙሉ ለሙሉ የዓይን መጥፋትን ጨምሮ በዓይን ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ጉዳቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን” አምነስቲ አስታውቋል፡፡
ጥናቱ በተካሄደባቸው አንዳንድ አገሮች ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች፣ የአጥንት፣ የራስ ቅል ስብራትና የጭንቅላት ጉዳት፣ እንዲሁም የውስጥ አካላት ጉዳት፣ ወይም በጎድን አጥንት በኩል በልብና ሳንባዎቻቸውን ላይ እክል የደረሰባቸው መሆኑን አምነስቲ ገልጿል፡፡
መሰረቱን ብሪታኒያ ካደረገው ኦሜጋ የጥናት ማዕከል ጋር በመተባበር ጥናቱን ያሳተመው አምነስቲ፣ የተገደሉ ተቃዋሚ ሰልፈኞች መኖራቸውንም አመልክቷል፡፡
እየተባባሰ የመጣውን የመብቶች ጥሰት ለመዋጋት፣ በመሳሪያዎቹ ምርትና ሽያጭ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በህግ አሳሪ የሆነ ቁጥጥር በአስቸኳይ እንዲደረግ የአምነስቲ ኢንተርናሽናሉ ተወካይ ፓትሪክ ዊልከን መናገራቸውንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡