በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሚሶም (AMISOM) አዛዥ በነዳጅ ማጭበርበር ተወነጀሉ


የአሚሶም የጦር መኪና በሶማልያ
የአሚሶም የጦር መኪና በሶማልያ

የቀድሞው የአሚሶም ወይም በሶማልያ የሚገኙ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ዋና አዛዥ ለሰላም ጥበቃ ተልዕኮ የሚውለውን ነዳጅ ለሌላ ተግባር አውለዋል፣ በሽያጩም ተጠቅመዋል ተብለው ተወነጀሉ።

በሶማልያ የሚገኙ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ዋና አዛዡ ከሰባት ሺህ ሊትር በላይ ናፍታ ነው ሸጠው ገንዘቡን በሉ የተባሉት። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአሚሶም ኃይሎች ምክትል አዛዥ በባርድሄር (Bardheere) እና በዲንሶር (Diinsor) ጉብኝት አረጉ። በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ወጣት ተማሪዎች አል-ሻባብን እየተቀላቀሉ መሆናቸውን የኬንያው መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሶማልያ ውስጥ በሚገኘው የአፍሪቃ ሕብረት (አሚሶም) ልዑክ ስር የቀድሞው የኡጋንዳ ሕዝባዊ መከላከያ ሠራዊት አዛዥ ሌፍትናንት ኰሎኔል እዩጂን ሰቡግዋዎ (Eugene Ssebugwawo), ነዳጅ ያለ አግባብ ለሌላ ተግባር አውለዋል ተብለው የ18 ወራት እስራት ተበይኖባቸዋል። እዩጂን ሰቡግዋዎ (Eugene Ssebugwawo)፣ የእስራት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከካምፓላ ወጣ ብሎ በሚገኘው በማኪንድዬ (Makindye) ወታደራዊ ፖሊስ ዋና ጽ/ቤት ውስጥ መሆኑም ታውቋል።

የፍርድ ቤቱ ሰብሳቢ ሜጀር ጅንናር ሌቪ ካሩሃንጋ (Levy Karuhanga) ብይኑን ሲሰጡ በተናገሩት ቃል፣ “የ18 ወር እስራት ተፈርዶብዎታል” ብለዋል። አክለውም፣ “በዚህ ውሳኔ ተቃውሞ ካለዎ፣ በ14 ቀን ውስጥ ይግባኝ ለማለት ህገ-መንግሥቱ ይፈቅድልዎታል” ብለዋል። ተከሳሹ እዩጂን ሰቡግዋዎ (Eugene Ssebugwawo) የተወነጀሉት፣ ከ7,000-8,000 ሊትር የሚሆን ናፍታ ሶማልያ ውስጥ በአፍሪቃ ሕብረት ስር ለሚገኘው የኡጋንዳ ሕዝባዊ መከላከያ ሠራዊት የሰላም ጥበቃ ኃይል እአአ ከሚያዝያ 2012-ግንቦት 2013 ባለው ጊዜ አዛውረዋል ተብለው ነው። በፍረደሪክ ካንግዋሙ (Fredrick Kangwamu) የሚመራው የክስ መዝገብ ሁኔታውን ሲያብራራ፣ እዩጂን ሰቡግዋዎ (Eugene Ssebugwawo) ነዳጅ በገንዘብ ሽጠው ሲያበቁ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ብሏል።

የአሚሶም ኃይሎች ምክትል አዛዥ በትናንቱ ዕለት በባርድሄር (Bardheere) እና በዲንሶር (Diinsor) ጉብኝት ማድረጋቸው ተገልጿል።

ሁለቱ የሶማልያ ከተሞች በባርድሄር (Bardheere) እና በዲንሶር (Diinsor) በቅርቡ ነፃ የወጡ ናቸው። ምክትል አዛዡ ሜጀር ጅንናር ሞሓሜዴሻ ዘይኑ በጉብኝታቸው ወቅት፣ ሠራዊቱ የአካባቢውን፣ ባጠቃላይ የሶማልያን አንድነትና ነፃነት እስከሚያስከብር ድረስ ከትግሉ እንዳይዘናጋ አሳስበዋል።

አዲሱ አበበ አቀናብሮ ያቀረበውን ሙሉውን ዘገባ የተያያዘውን የድምጽ ፋይል በመጫን ያዳምጡ።

የአሚሶም (AMISOM) አዛዥ በነዳጅ ማጭበርበር ተወነጀሉ /ርዝመት - 2ደ24ሰ/
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:24 0:00

XS
SM
MD
LG