በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ራዲዮ መፅሔት - ዕሁድ፤ ግንቦት 9-2012 ዓ.ም.


የዕሁድ፤ ግንቦት 9 / 2012 ዓ.ም. የቪኦኤ ዜና

በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ላይ የሕግ ምሁራን ማብራሪያ

የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ጊዜ መቀየሩ የፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ሕገመንግሥታዊ ትርጓሜ መጠየቅ ሕጋዊ አማራጭ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የባለሙያዎቹን አስተያየት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ትናንት፤ ቅዳሜ አዳምጧል።

ዝርዝሩን የያዘውን ዘገባ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

*** *** ***

ኮቪድ-19 ዛሬ፤ በኢትዮጵያና በዓለም

ኢትዮጵያ ውስጥ ለኮሮናቫይረስ መጋለጣቸው ከተገጋገጠ የዛሬ አሥራ አንድ ሰዎች ጋር አጠቃላዩ ቁጥር ውድ 317 ከፍ ማለቱን የጤና ሚኒስቴር በትዊተር ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል።

113 ሰዎች ከሕመሙ ስሜት የወጡ ሲሆን ከዚህ በጎ ዜና ጋር በተጨማሪ ሃገሪቱ አሁን ባለው ጊዜ በኮቪድ-19 በጠና የታመመ ሰው የላትም፤ አዲስ የኮቪድ-19 ሞትም የለም።

በሌላ በኩል ግን ባለፉት ከሃያ አራት ሰዓታት በላይ ለሆን ጊዜ ይህ ዜና እስከተጠናቀረ ድረስ የተሻለው ተጨማሪ ሰውም አልተመዘገበም።

በጤና ሚኒስቴሩ መግለጫ መሠረት ኢትዮጵያ እስካሁን በአጠቃላይ 317 ሰው ለአዲሲ ኮሮናቫይረስ ተጋልጦባታል፤ ሁለት ሰዎች ወደ ሃገራቸው ተሸኝተዋል።

ዓለምአቀፍ መረጃዎች የአጠቃላዩን ተጋላጭ ቁጥር 319 ብለው የመዘገቡ ሲሆን ሁለቱን ተሸኚዎች ጨምሮ ይሁን አይሁን ግን የጤና ሚኒስቴሩም፣ ዓለምአቀፍ ሠንጠረዦቹም አይናገሩም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመላው ዓለም ለአዲሱ ኮሮናቫይረስ የተጋለጠው ሰው ቁጥር 4 ሚሊየን 664 ሺህ 486 ሲሆን 312 ሺህ 327 ሰው በኮቪድ-19 ምክንያት መሞቱን የጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሮናቫይረስ መረጃ ማዕከል አስታውቋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 11 ሚሊየን 77 ሺህ 179 ሰው ተመርምሮ 1 ሚሊየን 471 ሺህ 674 ሰው ለቫይረሱ መጋለጡ የተረጋገጠ ሲሆን 88 ሺህ 811 ሰው በኮቪድ-19 ምክንያት ሞቷል።

ዩናይትድ ስቴትስን ተከትለው እንግሊዝ 34 ሺህ 546 ሰው፤ ኢጣልያ 31 ሺህ 763 ሰው ሞተውባቸዋል። ስፓኝ ከ27 ሺህ በላይ በተመዘገበ የኮቪድ-19 ሞት ሠንጠረዡ ላይ በአራተኛነት ሠፍራለች።

*** *** ***

ሶማሊያ - አገረገዥ ተገደሉ

ማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ በተፈፀመ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት በፑንትላንድ አስተዳደር ውስጥ የምትገኘውን ሙግዱድ ክልል ገዥን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተገድለዋል።

በቦምብ የታጨቀ መኪናውን አገረገዥ አህመድ ሙሴ ከነበሩበት መኪና ጋር ሆን ብሎ ባጋጨው አጥቂ አብረዋቸው የነበሩ ወንድማቸውና ሁለት ጠባቂዎቻቸው፣ እንዲሁም መንገድ ላይ ቆሞ የነበረ አንድ ሲቪልም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን አደጋው የተጣለባት የጋልካዮ ከተማ ከንቲባ ሰይድ ሙሃሙድ አሊ ለቪኦኤ ገልፀዋል።

ለጥቃቱ አልሻባብ ኃላፊነት ወስዷል።

*** *** ***

እሥራዔል - ኔታንያሁ ቃለመሃላ ፈፀሙ

የእሥራዔል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ዛሬ ለአዲስ አስተዳደራቸው ቃለመሃላ ፈፀሙ።

ኔታንያሁ የመጭ ጊዜ ሥራቸውን ዛሬ የጀመሩት ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ከተጓተተ የፖለቲካ አጣብቂኝና ውዝግብ በኋላ መሆኑ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ሥልጣናቸውን ከእርሣቸው ሊኩድ - የብሔራዊ አርነት ንቅናቄ ጋር ጋር ጥምር መንግሥት ለፈጠረው ሰማያዊና ነጭ ፓርቲ መሪ ቤኒ ጋንትዝ እንደሚያስረክቡም ታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር መለዋወጥ ሕገወጥ ነው ብለው የሚከራከሩ ተቃዋሚዎች እየተሰሙ ሲሆን ካቢኔው እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ የሚኒስትሮች ቁጥር - ሰላሣ ስድስት ሚኒስትሮች የሚገኝበት እንደሆነ ተገልጿል።

የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ቤተእሥራዔላዊ ሚኒስትርም መሾማቸው ተሰምቷል።

*** *** ***

እሥራዔል - የቻይና አምባሳደር ሞተው ተገኙ

በእሥራዔል የቻይና አምባሳደር ዱ ዌዪ ሄርዚልያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታችው ሞተው መገኘታቸውን የእሥራዔል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

አምባሳደር ዌዪ የተሾሙት ባለፈው የካቲት ነበር።

ጀሩሳሌም ፖስት ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ ሃምሣ ሰባት ዓመት ዕድሜአቸው ላይ የነበሩት የቻይና አምባሳደር የሞቱት “በድንገተኛ የልብ መታወክ ነው” ብለው መርማሪዎቹ እንደሚያምኑ ፅፏል።

*** *** ***

ትረምፕ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣን አባረሩ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከትናንት በስተያ ዓርብ ምሽት ላይ ማባረራቸውን ተከትሎ ዴሞክራቲክ እንደራሴዎች ምርመራ ጀምረዋል።

አቃቤ ሕጉ ስቲቭ ሊኒክ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፔዮ ላይ ምርመራ ከፍተው እንደነበረ ታውቋል።

በፕሬዚዳንቱ ላይ ተከፍቶ የነበረው የተወካዮች ምክር ቤቱ የክሥ ሂደት እርሣቸውን ነፃ በማውጣት ከተጠናቀቀ ወዲህ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ያሉ የመንግሥቱን ተቆጣጣሪዎች ሲያባርሩ ሊኒክ ሦስተኛው መሆናቸው ነው።

ሊኒክ የተሾሙት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ነበር።

ዋይት ሃውስ ከሊኒክ መባረር ጋር የተያያዙ ሠነዶችን ሁሉ እንዲያቀርብ እንደራሴዎቹ ጠይቀዋል።

የዕሁድ፤ ግንቦት 9/2012 ዓ.ም. የቪኦኤ የራዲዮ መፅሔት
please wait

No media source currently available

0:00 1:01:26 0:00


XS
SM
MD
LG