በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዦች ተገደሉ


በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዦች ተገደሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:56 0:00

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዦች ተገደሉ

በዐማራ ክልል፣ ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ የደጀን ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ሓላፊ እና ምክትላቸው፣ አንድ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ መገደላቸውን ዞኑ አስታወቀ። ዋና እንስፔክተር ዘውዱ ታደለ እና ምክትል ኢንስፔክተር ወርቁ ሽመልስን ገድሏቸዋል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ እስካሁን በቁጥጥር ስር እንዳልዋለ ፖሊስ ገልጿል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ሓላፊ ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንዳስታወቁት፣ ሁለቱ የፖሊስ አዛዦች የተገደሉት፣ ትላንት ሰኞ ከቀትር በኋላ፣ ለስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የጸጥታ ሥራዎችን ለመከታተል፣ ኩራር ወደ ተባለ ቀበሌ በመጓዝ ላይ እንዳሉ ነው። ግድያው፣ በክልሉ እየተካሔደ ካለው ግጭት ጋራ የተያያዘ ስለመኾኑ ግን፣ የተገለጸ ነገር የለም።

ሁለቱ የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዦች፣ ዓባይ በረሓ በሚገኘውና ኪዳነ ምሕረት ወይም “ግልገሌ“ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ እንደተገደሉ፣ በዐማራ ክልል የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ሓላፊ፣ ኮማንደር አያልነህ ተስፋዬ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

“የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት ሓላፊ እና ምክትላቸው፣ የወንጀል መከላከል ሓላፊዎች ናቸው፡፡ የስምንተኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥን ቁጥጥር እያደረጉና ሌሎችንም የጸጥታ ሥራዎች እየሠሩ ባለበት ሰዓት፣ የታጠቀ ግለሰብ ነው ግድያ የፈጸመባቸው፤” ያሉት አቶ አያልነህ፣ “ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ባይውልም ማንነቱ ተረጋግጧል፤ ክትትል እየተደረገበት ነው፤ ለግድያ ያነሣሣው ምክንያት በውል አልታወቀም፤ ግለሰቦቹ የተመቱበት አካባቢ ምንም ዐይነት የጸጥታ ችግር አልነበረበትም፤” ብለዋል።

የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ እና የምክትላቸው ግድያ ዜና የተሰማው፣ በዐማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር እልባት ባላገኘበት ወቅት ነው።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በሌሎች የታጠቁ አካላት፣ እንደዚኹም በነዋሪዎች እና በጸጥታ አካላት መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች፣ ሰላማዊ ሰዎች እና ሌሎችም እንደተገደሉ መዘገባችን ይታወሳል።

የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዦች በተገደሉበት ተኩስ፣ ሁለት የመኪና አሽከርካሪዎች እንደቆሰሉ የተናገሩት፣ የደጀን ወረዳ ሰላም እና ደኅንነት ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ካሳው አስፋው፣ “በመኪናው ውስጥ ሦስት ሰዎች ነበሩ፡፡ ሹፌሩ ቀላል ጉዳት ደርሶበት፣

ደብረ ማርቆስ ሆስፒታል ነው ያለው፡፡ አዛዞቹንና ሹፌሩን ከመታ በኋላ፣ ሌላ የመንገደኞች መኪና ሹፌር ለማስቆም ሲያስገድድ አልቆምለት ሲል ነው የመታው፤” ብለዋል።

በክልሉ የፖሊስ አዛዦች ግድያ፣ እየታየ ካለው ግጭት ጋራ የተያያዘ ስለመኾኑ፣ ለኮማንደር አያልነህ ላነሣነው ጥያቀ፣ ኮማንደሩ መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG