በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በማዳበሪያ እጥረት የተቆጡ አርሶ አደሮች አቤቱታ


በማዳበሪያ እጥረት የተቆጡ አርሶ አደሮች አቤቱታ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:51 0:00

በማዳበሪያ እጥረት የተቆጡ አርሶ አደሮች አቤቱታ

· የዐማራ ክልል በከፍተኛ የማዳበሪያ እጥረት መመታቱ ተገልጿል

የአፈር ማዳበሪያ ፍለጋ እየተንከራተቱ የዘር ወቅት ያለፈባቸውና ለረኀብ የመጋለጥ ስጋት ያደረባቸው፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ አርሶ አደሮች፣ የምሬት አቤቱታ አቀረቡ፡፡

ዞኑ የሚገኝበት የዐማራ ክልል፣ በከፍተኛ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት መመታቱ ተገልጿል፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን የደቡብ ሜጫ ወረዳ አርሶ አደሮች፣ “ማዳበሪያውን ካልሰጣችኹን ሌሎች አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን እንድትሰጡን አንፈቅድላችኹም፤” በሚል በወረዳው ባለሥልጣናት ላይ ቁጣቸውን እየገለጹ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡

በ10 ሺሕዎች በሚቆጠሩ የወረዳው አርሶ አደሮች ተወክለው ወደ ባሕር ዳር ግብርና ቢሮ የተላኩ ስምንት አርሶ አደሮች እና አንድ የወረዳው ባለሞያ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በዚኽ ወቅት የአፈር ማዳበሪያ ካላገኙ፣ በሚቀጥለው ዓመት ለረኀብ እንደሚጋለጡ አሳስበዋል፡፡

በክልሉ ከፍተኛ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት መኖሩን ያመነው፣ የዐማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ “ከፌደራል መንግሥት ጋራ እየተነጋገርኹበት ነው፤” ብሏል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፣ እጥረቱ የተከሠተው በመላ አገሪቱ እንደኾነ አመልክቶ፣የግብዓት ሥርጭቱ፥ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በወቅቱ ባለመድረሱ ችግሩ ማጋጠሙን አስረድቷል፡፡

ከዐማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ፣ ወደ ባሕር ዳር የክልሉ ግብርና ቢሮ መጥተው፣ አቤቱታ ሲያሰሙ ያገኘናቸው ስምንት አርሶ አደሮች እና አንድ የግብርና ባለሞያ፣ በወረዳው ከፍተኛ የማዳበሪያ እጥረት መከሠቱን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደር ጌቱ ታመነ፣ ከደቡብ ሜጫ ለሁሉ ሰላም ቀበሌ እንደመጡ ይናገራሉ፡፡ በየዓመቱ በቆሎ ይዘሩ እንደነበር የገለጹት አርሶ አደሩ፣ ዘንድሮ፣ ከግንቦት 1 እስከ 16 ቀን ድረስ ተዘርቶ ማለቅ ሲኖርበት፣ በአፈር ማዳበሪያ እጥረት የተነሳ እስከ አሁን አልተዘራም፤ ብለዋል፡፡

ከአርሶ አደሮቹ ጋራ አቤቱታ ለማሰማት ወደ ቢሮው የመጡት፣ የደቡብ ሜጫ ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት የግብአት ቡድን መሪ አቶ አለማ ዳኘው፣ በወረዳው፣ የአፈር ማዳበሪያ ባለመከፋፈሉ ቅር የተሰኘው አርሶ አደር መቆጣቱን አመልክተዋል፡፡ “አርሶ አደሩ ጅራፉን እንደያዘ፣ በመንግሥት ቢሮዎች ደጅ ነው የሚውለው፤” ብለዋል አቶ አለማ፡፡

ከቅሬታ አቅራቢ የወረዳው አርሶ አደሮች አንዱ ደጉ ካሳሁን፣ ማዳበሪያ ካላመጣችኹ አታገለገሉንም፤ ሲሉ፣ በአካባቢው ባለሥልጣናት ላይ ቁጣ እያሰሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የሰባታሚት ቀበሌ አርሶ አደሮችም፣ የአፈር ማዳበሪያ ለማግኘት መንከራተታቸው፣ በእርሻ ሥራቸው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን የደቡብ ሜጫ ወረዳ አርሶ አደሮች አቤቱታ፣ በዐማራ ክልል ደረጃ የሚታየው ከፍተኛ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ማሳያ እንጂ፣ በኹሉም የክልሉ አካባቢዎች፣ እጥረቱ መኖሩን አረጋግጠናል፡፡

የዐማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ አምሳሉ ጎባው እንደሚገልጹት፥ የክልሉ መንግሥት፣ 5ነጥብ2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት፣ ለግብርና ሚኒስቴር ጥያቄ ቢያቀርብም፣ እስከ አሁን የተላከው ግን፣ 1ነጥብ7 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው፡፡ ቀሪው 3ነጥብ5 ሚሊዮን ኩንታል በፍጥነት እንዲላክለት፣ ቢሮው፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በመነጋገር ላይ ነው፡፡

ስለ ጉዳዩ፣ በግብርና ሚኒስቴር የግብአት አቅርቦት ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ተስፋ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት የተከሠተው በመላ አገሪቱ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የችግሩ ዋና መንሥኤም፣ የግብአት ሥርጭቱ ቅደም ተከተልን ባለመጠበቁ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡

ለአገሪቱ በአጠቃላይ የሚያስፈልገው፣ ከ12 ሚሊዮን በላይ ኩንታል የማዳበሪያ ግዥ የተፈጸመ ሲኾን፣ ገሚሱ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱንና ገሚሱ ደግሞ በጅቡቲ ወደብ ላይ እንደሚገኝ፣ አቶ መንግሥቱ አስረድተዋል፡፡ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው ውስጥ፣ ከአራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ መከፋፈሉን አክለው ገልጸዋል፡፡

ለእርሻ ሥራው ወሳኝ ግብአት የኾነው የዳፕ እና ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት፣ በአጭር ጊዜ እንደሚፈታም፣ አቶ መንግሥቱ አመልክተዋል፡፡

XS
SM
MD
LG