በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደብረ ኤልያስ አንድነት ገዳም ግጭት በመቶዎች የተቆጠሩ መነኰሳት፣ ምእመናንና የመከላከያ አባላት መጎዳታቸው ተገለጸ


በደብረ ኤልያስ አንድነት ገዳም ግጭት በመቶዎች የተቆጠሩ መነኰሳት፣ ምእመናንና የመከላከያ አባላት መጎዳታቸው ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:13 0:00

በደብረ ኤልያስ አንድነት ገዳም ግጭት በመቶዎች የተቆጠሩ መነኰሳት፣ ምእመናንና የመከላከያ አባላት መጎዳታቸው ተገለጸ

በዐማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ደጎልማ ቀበሌ በሚገኘው፣ በደብረ ኤልያስ ብሔረ ብፁዓን መልክአ ሥላሴ አንድነት ገዳም ውስጥ እና አካባቢው በተፈጠረ ግጭት፣ ከሲቪሎችም ኾነ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል፣ በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎች መጎዳታቸውን፣ ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የደብረ ኤልያስ ወረዳ የሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት፣ ስለ ግጭቱ ባወጣው መግለጫ፣ ገዳሙ የታጣቂዎች መሸሸጊያ በመኾኑ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በገዳሙ ውስጥ ልዩ ዘመቻ ማድረጉንና በገዳሙ ላይ ጉዳት አለመድረሱን ገልጿል።

ለጸበል በገዳሙ ውስጥ እንደነበርና “ውጊያ” ሲል በጠራው ግጭት በደረሰበት የጥይት ምት እግሩን መቆረጡን፣ በደንበጫ ከተማ በሕክምና እየተረዳ የሚገኝ አንድ ታካሚ ነግሮናል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የደብረ ኤልያስ ሆስፒታል ሐኪም፣ ካለፈው ሳምንት ኀሙስ ጀምሮ፣ ከ200 የማያንሱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ቆስለው ወደ ሆስፒታሉ መግባታቸውንና ከእነርሱም ውስጥ 10 ያህሉ ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸውልናል።

በጉዳዩ ላይ፣ የአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ፣ ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፥ ጉዳዩን አጣርቶ በቅርብ ቀን ለምእመኑ ሙሉ መረጃ ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።

በዐማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ በደጎልማ ቀበሌ በሚገኘው፣ የደብረ ኤልያስ ብሔረ ብፁዓን መልክአ ሥላሴ አንድነት ገዳም ውስጥ፣ ከፍተኛ ግጭት መከሠቱ የተሰማው፣ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን፣ የደብረ ኤልያስ የመጀመሪያ ሆስፒታል ሐኪም፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ ካለፈው ኀሙስ ጀምሮ እስከ ትላንት ወዲያ ድረስ፣ ወደ ሆስፒታሉ ለመጡ ከ200 በላይ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ የሕክምና ርዳታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ቆስለው ከመጡት የጸጥታ ኃይሎች መካከልም፣ የ10 ያህሉ ሕይወት ማለፉን አስታውቀዋል፡፡

በግጭቱ ቆስለው ወደ ሆስፒታሉ ከገቡት ውስጥ፣ ከመንግሥት የጸጥታ አባላት በቀር፣ ንጹሐን ዜጎችን አለማየታቸውን፣ ሐኪሙ አክለው ገልጸዋል።

በገዳሙ ውስጥ፣ ከአንድ ዓመት በፊት፣ ጸበል ለመጸበል ገብተው ፈውስ በማግኘታቸው፣ እስካለፈው ማክሰኞ ድረስ፣ በገዳሙ መቆየታቸውንና አሁን ግን በተደረገው ውጊያ ምክንያት፣ አንድ እግራቸው ተቆርጦ በደንበጫ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተደረገላቸው ያሉ ታካሚ፣ ለአሜሪካ ድምፅ የነበረውን ኹኔታ ሲያብራሩ፣ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ ሌሊት ላይ ወደ ገዳሙ ከባድ መሣሪያ መተኮስ መጀመሩንና ይኸው ተኩስ ውሎ አድሮ እስከ ማክሰኞ መዝለቁን ተናግረዋል፡፡

ካለፈው ሳምንት ዐርብ ጀምሮ፣ ከገዳሙ በቅርብ ርቀት ከምትገኘው ገነቴ ከተባለችው ቀበሌ ኾነው በዙሪያው የተካሔደውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተመልክቻለኹ፤”

በብሔረ ብፁዓን መልክአ ሥላሴ አንድነት ገዳም ውስጥ፣ በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩ ከ500 እስከ 600 ማኅበረ መነኰሳት፣ የአብነት ተማሪዎች እና ሌሎች ማኅበረ ምእመናን በቋሚነት እንደሚኖሩበት ይገመታል፤ ያሉት፣ እኚኹ ጉዳተኛ ታካሚ፣ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ጸበልተኞችም በቅጽሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ካለፈው ሳምንት ኀሙስ እስከዚኽ ሳምንት ማክሰኞ በነበረው የከባድ መሣሪያ ድብደባ፣ ብዙ መነኰሳት እና የአብነት ተማሪዎች፣ እንዲሁም ጸበልተኞች ለሞት እና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ ከድብደባው ተርፈው በገዳሙ አቅራቢያ ወደሚገኘው ተምጫ ወንዝ የተሰደዱትም፣ በምን ኹኔታ ላይ እንዳሉ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

በእርሳቸውም ላይ ጉዳት ስለደረሰበት ኹኔታ ሲያስረዱ፣ ማክሰኞ ዕለት ወደ ገዳሙ በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ አንድ እግራቸው መቆረጡንና በደንበጫ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደኾነ ጠቁመው፣ ከእርሳቸው ጋራ ሦስት የአብነት ተማሪዎች ቆስለው ወደ ሆስፒታል መግባታቸውንና ከእነርሱም ሁለቱ፣ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ደብረ ማርቆስ መላካቸውን ጠቁመዋል፡፡

“ካለፈው ሳምንት ዐርብ ጀምሮ፣ ከገዳሙ በቅርብ ርቀት ከምትገኘው ገነቴ ከተባለችው ቀበሌ ኾነው በዙሪያው የተካሔደውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተመልክቻለኹ፤” ያሉት፣ ሌላው የዐይን እማኝ አቶ ጌትየ ያለው፣ ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ የመከላከያ ከባድ ተሽከርካሪዎች በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡

በግጭቱ ቆስለው በደንበጫ ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ ያሉት ግለሰብ አያይዘው እንደሚሉት፣ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ “ፋኖ በገዳሙ ውስጥ አለ፤” ሲሉ እንደሰሟቸው ተናግረዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ሌላው የአካባቢው ነዋሪ፣ ወደ ቀበሌዋ የገቡ የሀገር መከላከያ ኃይሎች፣ ወደ ገዳሙ ተኩስ መክፈታቸውንና በዚኽም ሳቢያ፣ በገዳሙ ውስጥ የነበሩ መነኰሳት፣ እንዲሁም ሴቶች እና ሕፃናት መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡

ነዋሪነታቸው በደብረ ማርቆስ ወረዳ የኾኑና የገዳሙን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ ሌላ ነዋሪ፣ የአንድነት ገዳሙ፣ ከደብረ ኤልያስ ወረዳ ጽ/ቤት እና ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ጋራ፣ አለመግባባት

እንዳላቸው እንደሚያውቁ ጠቅሰው፣ መንሥኤውም በአንጋቾች ይጠበቃሉ ከሚባሉትና የማጥመቅ አገልግሎት ከሚሰጡት አባት ጋራ እንደሚያያዝ ተናግረዋል፡፡

የደብረ ኤልያስ ወረዳ ጽ/ቤት፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፣ ገዳሙ፥ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመግደል ተጠያቂ የኾኑ የተወሰኑ ታጣቂዎች፣ በሕግ ላለመጠየቅ መሸሸጊያ እና ወታደራዊ ማሠልጠኛ ኾኗል፤ ሲል ጠቅሷል፡፡ የገዳሙ አባቶች፣ ይህን ድርጊት እንዲያስቆሙ መጠየቁንም አውስቷል፡፡

ወረዳው በመግለጫው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በገዳሙ ውስጥ ልዩ ዘመቻ በማድረግ አስፈላጊውን ርምጃ መውሰዱንና በገዳሙ ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ግዛቸው ስለወንድም፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በደብረ ኤልያስ ብሔረ ብፁዓን መልክአ ሥላሴ አንድነት ገዳም የተፈጠረውን ችግር፣ ወደ ቦታው ተጉዘው ለማጣራት፣ በመጪው እሑድ ዕቅድ ተይዟል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ፣ ትላንት ማምሻውን በፌስቡክ ገጹ እንዳስታወቀው፣ የደብረ ኤልያስ ብሔረ ብፁዓን መልክአ ሥላሴ አንድነት ገዳምን በተመለከተ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ገዳማት አስተዳደር መምሪያ፣ ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ጋራ በመገናኘት፣ ተፈጸመ የተባለውን ችግር በተመለከተ በዝርዝር የማጣራት ሥራ እያከናወነ ይገኛል፤ ብሏል፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትም፣ በማዕከል ደረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ ጠቅሶ፣ ዝርዝር ኹኔታውን በቅርቡ ለምእመናን እንደሚያሳውቅ አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG