በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በእስቴ ወረዳ አጎና ቀበሌ ግጭት አምስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ


በእስቴ ወረዳ አጎና ቀበሌ ግጭት አምስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:42 0:00

በእስቴ ወረዳ አጎና ቀበሌ ግጭት አምስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ አጎና ቀበሌ፣ ባለፈው ሰኞ፣ በፋኖ ታጣቂ ቡድንና በመንግሥት ኀይሎች መካከል ግጭት መካሔዱን ተከትሎ አምስት ያልታጠቁ ሰዎች መገደላቸውን፣ የተጎጂ ቤተሰቦች እና የዐይን እማኝ ነን ያሉ ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። እነዚህ ያነጋገርናቸው ሦስት ነዋሪዎች፣የራሳቸውን ጨምሮ 15 በሳር እና በቆርቆሮ የተሠሩ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ገልጸዋል፡፡ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በጉዳዩ ላይ፣ በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕርግ የአስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላም እና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም በፌደራሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም ስልካቸው ባለመመለሱ ምላሽ ለማግኘት አልቻልንም፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ በአጎና ቀበሌ፣ ባለፈው ሰኞ፣ ሚያዚያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በመንግሥት ኀይሎች እና በፋኖ ቡድን ታጣቂዎች መካከል የተካሔደውን ግጭት ተከትሎ፣ አንድ የ12 ዓመት ሴት አዳጊን ጨምሮ አምስት ያልታጠቁ ዜጎች መገደላቸውንና መኖሪያ ቤቶችም መቃጠላቸውን፣ የተጎጂ ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

የአጎና ቀበሌ ነዋሪ መኾናቸውን የገለጹልን አቶ አጥናፍ ዋለልኝ የተባሉ አስተያየት ሰጭ፣ እመቤት አጥናፍ የተባለች የ12 ዓመት ልጃቸው ውኃ ቀድታ ስትመለስ በመንግሥት ኀይሎች መገደሏን አስረድተዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ መኩሪያ የተባሉ ሌላው የዚኹ ቀበሌ ነዋሪ፣ በዕለቱ ከማለዳው ጀምሮ የተኩስ ድምፅ ሲሰሙ ማርፈዳቸውንና ኋላም የዕድር አባሎቻቸው መገደላቸውን ሰምተው ከቤት መውጣታቸውን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ሠራዊቱ በንጹሐን ዜጎች ላይ ግድያ ፈጽሟል፤ የሚሉ አቤቱታዎችን፣ በተለያዩ ጊዜያት በመንግሥታዊ ብዙኀን መገናኛዎች ቀርበው በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ማስተባበላቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በተለያየ ጊዜ ባወጣቸው መግለጫዎች፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የቀጠሉ ግጭቶች፣ በንጹሐን ዜጎች ላይ ጉዳት እያስከተሉ መኾናቸውን ጠቅሶ፣ ግጭቶቹ ሰላማዊ እልባት እንዲበጅላቸው ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG