በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጋዜጠኞች ላይ የተነጣጠረ ጥቃት በየጊዜው እየከፋ ነው


በጋዜጠኞች ላይ የተነጣጠረ ጥቃት በየጊዜው እየከፋ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:06 0:00

በጋዜጠኞች ላይ ከሚፈጸሙ 10 ግድያዎች ዘጠኙ ተጠያቂ አይደረጉም። ሴት ጋዜጠኞች ለዛቻ ይበልጥ እየተጋለጡ ነው፡፡ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን፣ የ2023ቱን የዓለም የፕሬስ ነፃነት አያያዝ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ዓመታዊው የፕሬስ ነፃነት አያያዝ ሪፖርት፣ በዓለም ዙሪያ በብዙኃን መገናኛ ላይ የሚነጣጠሩ ጥቃቶች እያደር እየጨመሩ መምጣታቸውን ያሳያል።

ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters without Borders) እ.አ.አ. በ2022፣ በዓለም ዙሪያ ያለውን የፕሬስ አያያዝ አስመልክቶ፣ አጠቃላይ ቅኝታዊ ጥናት ከአደረገባቸው 180 አገሮች ውስጥ፣ ከመቶ በሰባ እጁ፣ ችግር እንዳለበት የሚያመለክት እንደኾነ ጠቁሟል፡፡

የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን የዩናይትድ ስቴትስ ቢሮ ዋና ድሬክተር ክሌይተን ዊመርስ፤ “እንደ እኛ ቆጠራ፣ በዓለም ዙሪያ 533 ጋዜጠኞች እስር ገጥሟቸዋል።” ብለዋል።

በዓለም ዙሪያ ለጋዜጠኞች ኹኔታውን የከፋ የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ደግሞ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) እያጠናከረ ያመጣው የሐሰት መረጃ ሥርጭት መኾኑን ገልፀዋል።

በመጋቢት ወር ሞስኮ፣ ለዎል ስትሪት ጋዜጣ የሚዘግበውን አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ኢቫን ጌርሽኮቪችን፣ በስለላ ድርጊት ወንጅላ አሰረች። ጌርሽኮቪች ግን ውንጀላውን አስተባብሏል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ፣ በብዙኃን መገናኛ ላይ የምትወስደው ርምጃ መጠናከሩንና ቀድሞ ከነበረችበት ዘጠኝ ደረጃዎች ዝቅ ብላ ወደ 164ኛ ደረጃ መውረዷንም የጠቆሙት ዊመርስ ፤“ያየነው ነገር ቢኖር፥ በበይነ መረብ በሚቀርቡ መረጃዎች ስለ ጦርነቱ በመናገር ወይም ጦርነቱን የተመለከተ ነገር

በመጥቀስ ብቻ በጋዜጠኞች የመዘገብ ነፃነት ላይ የተነጣጠሩ በጅምላ የሚወሰዱ ርምጃዎችን ነው።” ይላሉ።በተጨማሪም፣ “ዩክሬን ውስጥ ጦር ሜዳ ላይ የሩስያ ኃይሎች በብዙኃን መገናኛ ላይ የተነጣጠሩ ጥቃቶችን ሲፈጽሙና በዚኽም ስምንት ጋዜጠኞችን ሲገደሉ ተመልክተናል።” ብለዋል።

በምሥራቅ እስያም በተመሳሳይ፣ በጋዜጠኞች አያያዝ የደረጃ ሰንጠረዥ ከከፋው የሚመደቡ አንዳንድ አገሮች አሉበት። በዓመታዊው የሀገራት የደረጃ ዝርዝር፣ 178ኛ ደረጃ የያዘችው ቬዬትናምም፣ በጋዜጠኞች እና በአስተያየት ሰጪዎች ላይ ርምጃ ስትወስድ ተስተውላለች።

ቻይናንና ሰሜን ኮሪያን በተመለከተ፣ አስተያየት የሰጡት ዊመርስ “ነፃ ፕሬስ የለም። በአጭሩም በቃ! ኖሮ አያውቅም።” ብለዋል።

በኢራን፣ በ“ሞራል ፖሊሶች” ከታሰረች በኋላ ለኅልፈት በተዳረገችው ማህሳ አሚኒን ግድያ የተነሣሣውን ተቃውሞ ጋዜጠኞች በመዘገባቸው ብርቱ ጫና ገጥሟቸዋል።

ባለፈው ዓመት፣ የአፍሪካ የብዙኃን መገናኛ ነፃነት አያያዝ ደረጃም በተመሳሳይ ቀንሶ ታይቷል።

በላቲን አሜሪካም፣ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን፣ “ጋዜጠኞች ሲገደሉ ተጠያቂነት የለም!” ያለውን በማመላከት የማስጠንቀቂያ ድምፅ አሰምቷል።

“ይህ ደግሞ በዋናነት፣ የሕግ የበላይነት ከመሠረቱ አደጋ ላይ በወደቀባቸው እንደ ሜክሲኮ ባሉ አገሮች የሚመራ ነው።” ሲሉ ዊመርስ አክለዋል።

ባለፈው መስከረም፣ በስለት ተወግቶ የተገደለው ጀርመናዊው የምርመራ ጋዜጠኛ ግድያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሰንጠረዡ ቀድሞ ከነበረችበት ሦስት ደረጃዎች እንድትወርድ አስተዋፅኦ አድርጓል።

የናሽናል ፕሬስ ክለብ ፕሬዚዳንት ኦይሊን ኦራሌ፤ የጋዜጠኞችን ሚና ያዋደቁባቸው ወይም የኃይል ጥቃት ፈጽመው የተገኙባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ ገልፀው “ለዚኽም ምክንያቱ፣ መረጃው እንዳይወጣ አፍኖ ለማስቀረት ስለሚሞክሩ እና ይዘቱን ለመቆጣጠር ስለሚፈልጉ ነው።” ብለዋል።

የብዙኃን መገናኛ ነፃነትን ለማስጠበቅ፣ “ተጠያቂነት ቁልፍ ነው” ሲሉ፣ አስተያየት የሰጡት የዩኔስኮው ጊልርሚ ካኔላ ፤ “አንዳንድ አገሮች የሚወስዱት የቅጣት መጠን፣ 99 በመቶ ይደርሳል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ስሌት 86 በመቶ ነው። ይህም እጅግ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል።” ብለዋል።

አያይዘውም “በጋዜጠኞች ላይ ከሚፈጸሙ 10 ግድያዎች ዘጠኙ፣ ተጠያቂ ሳይደረጉ ይቀራሉ። በመኾኑም፣ በዓለም አቀፉ ሥርዓት፣ በተጨባጭ እውን ልናደርግ የሚገባን የመጀመሪያው ነገር፣ ይህን መጠነ ሰፊ የመከላከል፣ ከለላ የመስጠት እና ለፍርድ የማቅረብ አሠራር ነው።” ብለዋል።

እንደ ዩኔስኮ ገለጻ፣ በዲጂታል መስኩ፣ ሴት ጋዜጠኞች እየጨመረ ለመጣ ዛቻ የተጋለጡ ሲኾን፤ በአንዳንድ ኹኔታዎችም አካላዊ ጥቃት ጭምር እየደረሰባቸው ነው።

XS
SM
MD
LG