በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ ድምጽ የስርጭቱን ይዞታ እስኪያሻሽል የኢትዮጵያ መንግስት ትብብር አላደርግም አለ


“መንግስቱ የማይወዳቸውን ድምጾች አለማሰማት አይቻልም” ቪኦኤ

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ስርጭቱን እንዲያስተካክልና የኢትዮጵያ መንግስትን የሚቃወሙ ድምጾችን እንዲመጥን ከኢህአዴግ አስተዳድር አቤቱታ ቀረበበት።

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮን የሚያስተዳድረው ቦርድ (Broadcasting Board of Governers) በኢትዮጵያ ባደረገው የስራ ጉብኝት ከኮሚውኒኬሽንስ ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖንና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረገው ውይይት ነው ወቀሳው የቀረበው።

ከግራ ወደቀኝ፣ ሱዛን መኩ፣ ዴና ፐሪኖ፣ በረከት ስምዖንና ማይክል ሚሃን በአዲስ አበባ
ከግራ ወደቀኝ፣ ሱዛን መኩ፣ ዴና ፐሪኖ፣ በረከት ስምዖንና ማይክል ሚሃን በአዲስ አበባ

በፕሬዝደንት ኦባማ ተወክሎ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮን የሚያስተዳድረው ቦርድ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነትና ትብብር ለማጠናከር፣ የመገናኛ ብዙሃን አቅም ግንባታ ላይ ለመሳተፍና፣ ተጨማሪ ዜናን ለመሰብሰብ የሚያስችለውን አቅም ለመገንባት በማሰብ ነው ወደ ኢትዮጵያ ያቀናው።

በፕሬዝደንት ቡሽ አስተዳድር የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ የነበሩት የቦርድ አባል ዴና ፐሪኖ፣ ሱዛን መኩና ማይክል ሚሃን ከሌሎች የቪኦኤ ሰራተኞች ጋር ነው ኢትዮጵያን የጎበኙት።

በዚህ ጉብኝት ከኮሚውኒኬሽንስ ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖንና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይቷል፣ የተለያዩ የሬድዮ ጣቢያዎችንም ጎብኝቷል።

ገቨርነር ዴና ፐሪኖ የቪኦኤ አጋር የሸገር ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያን ሲጎበኙ
ገቨርነር ዴና ፐሪኖ የቪኦኤ አጋር የሸገር ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያን ሲጎበኙ

የኢትዮጵያ መንግስትና የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ያላቸውን የሻከረ ግንኙነት በማሻሻልና፤ በተለይ አለም አቀፍም ሆነ አገራዊ ህጎችን በሚጻረር መልኩ የአማርኛ፣ ትግርኛና ኦሮሚኛ ቋንቋ ስርጭቶችን ማፈኑ እንዲቆም፤ የዝግጅት በክፍሎቹ የዜና መረባቸውን በክልሎች እንዲያስፋፉ ይፈልጋል የአሜሪካ ድምጽ።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ የአሜሪካ ድምጽ ዘገባዎች ሚዛናዊ ያልሆኑ፤ ለተቃዋሚዎች ያደሉና፤ የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባርን የጠበቁ አይደሉም ሲል፤ ከዚህ ቀደም ሲከስ ቆይቷል።

በቪኦኤ ቦርድ ከአቶ በረከት ስምዖን ጋር የተደረገው ውይይት በሚኒስትሩ ንግግር ነበር የተከፈተው።

ከልዑካኑ ጋር አብሮ የተጓዘው የአሜሪካ ድምጽ የአፍሪካ ቀንድ ዝግጅት ክፍል ስራ አስኪያጅ ዴቪድ አርኖልድ የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ አበባ ለሚገኘው የዩናይትድ ስቴይትስ ኢምባሲ የባለ 41 ገጽ ክስ ከሳምንታት በፊት አቅርቦ እንደነበረ ይናገራል።

ሰነዱ ባለፉት ጥቂት ወራት የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ስርጭቶች ያስተላለፏቸውን ዘገባዎች ተቃዋሚ ዘመምነት ያሳያሉ በሚል የቀረቡ አብነቶችን አካቷል።

“የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የሚያቀርባቸው እንግዶች ለኢትዮጵያ መንግስት በጎ አመለካክት የላቸውም፤ አንዳንዶቹ ጽንፍ የረገጡ ተቃዋሚዎች ናቸው” ይላል የኢትዮጵያ መንግስት ክስ እንደ ዴቪድ አርኖልድ ገለጻ።

“ጥያቄው አሁንና ቀድሞ በፖለቲካ የተሳተፉና ከኢትዮጵያ መንግስት የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች ሃሳብና ራእይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማሰማት እንችላለን የሚል ነው መሰረቱ። ይህ ከሆነ የአቶ በረከት ተቃውሞ ስራችንን ያከብደዋል” ብሏል ዴቪድ አርኖልድ።

የቪ ኦ ኤ ቦርድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የጀመረውን ውይይት እንደሚቀጥልበትና ተስፋ ሰጭ ጅምር እንደሆነ ዴቪድ አርኖርድ ተናግሯል።

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በኢትዮጵያ ያለው ተሰሚነት አሁን ካለበት ከፍተኛ ድረጃ እንዲጨምር፣ የዜና ዘገባዎቹ ሚዛናዊና የታመኑ እንዲሆኑ በሚያደርገው ጥረት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሚኖር ትብብር ወሳኝ መሆኑን ዴቪድ አርኖልድ ያሰምርበታል።

በዚህ ጥረት የኢትዮጵያ መንግስት ትብብር እንደሚያደርግ ተናግሯል። ሆኖም የቅድመ-ሁኔታ ተቀምጧል። ይሄ ቅድመ-ሁኔታ የአሜሪካ ድምጽ አዘጋገቡን እስኪያስተካክል ድረስ የኢትዮጵያ መንግስትን ትብብር አያገኝም የሚል ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግስትን ምላሽ ለማግኘት አቶ በረከት ስምዖን ጋር ደውለን፤ “ዝግጅቶቻችሁን እስከምታሻሽሉ” መግለጫ መስጠት አንችልም ብለውናል።

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ወደ ኢትዮጵያ ማስራጨት ከጀመረ 28 ዓመታት ተቆጥረዋል። በአሁኑ ወቅት በበርካታ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዝግጅቱን እንደሚከታተሉ ይታወቃል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG