በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኤርትራ ላይ የኢኮኖሚ ማእቀብ ጣለ


በውጭ አገር የሚኖሩ ኤርትራዊያን የሚከፍሉት ቀረጥና የማእድን ገቢዋን ለአፍራሽ ተግባር እንዳይውል ያቅባል

ሰኞለት ሙሉቀን በተካሄደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ጉባዔ በኤርትራ መንግስት ላይ ተጨማሪ ማእቀብ ተጥሏል።

የተ.መ.ድ. ስምምነት ቁጥር 2023 የተባለው የዛሬው ማእቀብ በኤርትራ የማእድን ኢንዱስትሪና በውጭ አገር የሚኖሩ ኤርትራዊያን የሚከፍሉት ቀረጥ ለአፍራሽ ተግባር እንዳይውል ያቅባል።

ከዚህ ቀደም የመንግስታቱ ድርጅት ስምምነት 1907 በኤርትራ ላይ የጦር መሳሪያና በኤርትራ ባለስልጣናት የጉዞና የገንዘብ ዝውውር ማእቀብ ማሳለፉ ይታወሳል።

ተከታታይ ማእቀቡ ለንም እንዳስፈለገ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከአዲስ አበባ በቪዲዮ መልእክት ለጸጥታው ምክር ቤት አስታውቀዋል።

“እኛ የአካባቢው አገሮች በኤርትራ ውስጥ ስላለው የአገር ውስጥ አስተዳድር ግድፈት ልናወራ አይደለም የተሰበሰብንው። በዚያ ላይ የየራሳችን አቋም አለን። ልንደሰትም ልንጠላውም እንችላለን። ይሄን ጉዳይ ከምክር ቤቱ ፊት ቀርበት ማብራራት አያስፈልገንም ነበር። የኤርትራ መንግስት ግን የአካባቢውን አገሮች በአለመረጋጋትና በሽብር እያመሰ ነው።”

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በአስመራ የሚገኙ ጥቂት ፖለቲከኞች የምስራቅ አፍሪካን አገሮች በጠብ አጫሪነትና በሽብር ሊያፈራርሱ ተነስተዋል ሲሉ ወንጅለዋል።

ከአዲስ አበባ በቪዲዮ መገናኛ ድምጻቸውን ያሰሙት የአካባቢው መሪዎች፤ የጅቡቲ ፕሬዝደንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ፣ የሶማሊያው የሽግግር መንግስት ፕሬዝደንት ሼክ ሼሪፍ ሼክ አህመድ፣ የኬንያ የውጭጉዳይ ሚኒስትር ሞሰስ ዌታንጉላ፣ የዩጋንዳና የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ናቸው።

የጅቡቲው ፕሬዝደንት በንግግራቸው፤ በሰሜናዊ ግዛት ከኤርትራ ጋር የተከሰተውን የድንበር ግጭት አንስተዋል። ጁቡቲ የኤርትራ መንግስት ድንበር ተሻግሮ ወታደሮቹን በግዛሬ አስፍሯል ስትል ትወቅሳለች።

በኤርትራና ጂቡቲ ድንበር ራስ ዱሜራና አካባቢ ኤርትራ ጦሯን አለማስገባቷን ስትገልጽ የቆየች ቢሆንም፤ ቆይቶ በቃታር መንግስት ሸምጋይነት ባለፈው አመት ሰኔ ወር የቃታር ወታደሮች አካባቢውን እንዲቆጣጠሩ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። የጅቡቲ ፕሬዝደንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ድርድሩ መስተጓጎሉን የጸጥታው ምክር ቤት አስረድተዋል።

“ይህንን ስምምነት መፈራረማችንና የቃታር ወንድሞቻችን ልፋት የኤርትራን መንግስት አስተዳድር አስተሳሰብ አልለወጠም። አገሬን አሁንም እንደጠላት በመቁጠር መረጋጋት እንዳይኖር ሲጥሩ ይታያሉ። ወጣት ጅቡቲያዊያንን በአፈናና አስገድደው ወታደር በማድረግ፤ ተመልሰው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሽብር ስራ በምድራችን ላይ እንዲያከናውኑ ሰርጎ ያስገባል”

የሶማሊያው የሽግግር መንግስት ፕሬዝደንት ሼክ ሼሪፍ ሼክ አህመድ ደግሞ፣ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው በዩናትድ ስቴይትስ የስለላ ድርጅትና ሌሎች የአፍሪካ አገሮችና ብህረቶች የሚወቀሰውን አልሸባብን ኤርትራ ትደጋፋለች ሲሉ ይከሳሉ።

“አልሸባብና አልቃይዳ የፖለቲካና የእንቅስቃሴ ማስተባበርና መምራት ስልጠና ከኤርትራ መንግስት ያገኛሉ። ከዚያም በተጨማሪ በገንዘብና መሳሪያም ትደግፋለች። ይሄ ድጋፍ በየብስ በባህርና በአየር ወደ ሶማሊያ ይገባል። ይሄንን የምናውቀው በኤርትራ የሚገኘው ዳሂር አዌስ በአውሮፕላን ወደሶማሊያ ገብቷል። ስለዚህ የኤርትራ መንግስት ሶማሊያ ውስጥ የግንኙነት መስመርና አቅሙም አለው ማለት ነው”

የኬንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሰስ ዌታንጉላን በአፍሪካ ህብረት የዩጋንዳ አምባሳደር ሙሌ ኪቴንዴም ኤርትራ በተለይ በሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን አልሸባብን በመርዳት በአካባቢው ሽብር ትነዛለች ሲሉ ከሰዋል።

ኬንያ ውስጥ በቅርቡ የደረሱ ፍንዳታዎች፣ በሰሜን ኬንያ የሚገኙ የስደታኛ ጣቢያዎች ላይ በኬንያዊያን፣ በውጭ አገር የእርዳታ ሰራተኞችና በሶማሊያዊያን ስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በአልሸባብ የተቀናበሩ መሆናቸውን የኬንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ሞሰስ ዌታንጉላ አብራርተዋል።

“የጸጥታው ምክር ቤት ሁኔታውን አውሮና መርምሮ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል። በምስራቅ አፍሪካ አገሮች ህብረት (ኢጋድ) አባል አገሮች በሙሉ ድምጽ የቀረበውን ውሳኔ እንድታጸድቁ እጠይቃለሁ። ይሄ ውሳኔ በጥቂቱም ቢሆን ኤርትራ ወደ ህግ አክባሪነት እንድትመጣ ብለን እናምናለን።”

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዱ ለቪኦኤ ሲናገሩ ኤርትራ ጥፋተኝነት እስኪረጋገጥ ነጻ የመሆን መብቷ ተገፏል ብለዋል። የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ቢጋበዙም፤ በስብሰባው ለመገኘት የአሜሪካ መንግስት ፈቃድ መከልከሉን አቶ አሊ አስታወቀው፤ በጠቅላላ ማእቀቡን አውግዘዋል።

“እንዲህ ያለ አጥፊ ማእቀብ ለመጣል መቻኮል ፈጽሞ አያስፈልግም። ስምምነቱ በኤርትራ ህዝብና በመላው የአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች ላይ ተጨማሪ ሰቆቃ እንዲኖር የታሰበበት ማእቀብን የያዘ ነው። እንኳን መረጋጋትን በአፍሪካ ቀንድ ሊያመጣ ጭራሽ ሁኔታውን ወደ ብጥብጥ የሚመራ አካሄድ ነው የተያዘው።”

ይሄንን ማእቀብ ዩናይትድ ስቴይትስና አጋሮቿ በህብረት በኤርትራ ላይ ማሰናዳታቸውንና፤ በኤርትራ ላይ የሚነሱ ወቀሳዎችና ውንጀላዎችም ፍጹም እውነታ የሌላቸው መሆኑን በገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ፤ መረጋገጡን አቶ አሊ አብዱ ይናገራሉ።

ሆኖም የኤርትራን ሁኔታ እንዲያጣራ በተባበሩት መንግስታት የተሰየመው የሁኔታ መርማሪ ቡድን፤ ኤርትራ በሶማሊይ ውስጥ ለአልሸባብ እርዳታ እንደምትሰጥና በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ፈንጅ ለማፈንዳት መሞከሯን አጣርቶ ፈርዷል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ የኤርትራ ችግር ያለመግባባት ሳይሆን በአስመራ የሚገኝ “ጠብ አጫሪ ቡድን” የአስተሳሰብ ችግር ነው። አቶ መለስ በዚህም የኤርትራን መሪዎች “ከሽምቅ ውጊያ አስተሳሰብ ያልወጡ ጠብ እጫሪዎች “ ሲሉ ፈርጀዋቸዋል።

“ኤርትራ በመጀመሪያ የየመንን የሃኒሽ ደሴት ወረረች፤ በተኩስ ጀምራ…ወደ ድርድር አመራች። የኛን መሬት ወረረች፤ ከዚያ ውይይት ተጀመረ። የጅቡቲን መሬት ወረረች፤ እንዲያውም ጦር አላስገባሁም ብላ ስትክድ ከቆየች በኋላ የቃታር ወታደሮች ቦታውን ይቆጣጠሩ ብላ አካባቢውን ስትለቅ፤ ቀድሞውንም መውረሯ ተረጋገጠ።”

አቶ መለስ አክለውም በኬንያ፣ በዩጋንዳ፣ በሶማሊያና በሱዳንም ኤርትራ በቀጥታና በእጅ አዙር ጦር በመምዘዝና በማሸበር አስቸግራናለች ሲሉ ለአለሙ ድርጅት አቤት ብለዋል።

በዚህ ውሳኔ ላይ ሌሎች አባላት ድምጻቸውን ሲሰጡ ቻይናና ራሻ ድምጽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG