በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤርትራ የተባበሩት መንግስታት ተጨማሪ ማእቀብ የጣለብኝ ለዩናይትድ ስቴይትስ ስለማላጎበድድ ነው አለች


ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቪዛ ማግኘታቸውን ዩናይትድ ስቴይትስ ገለጸች

በኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማእቀብ ከመጣሉ በፊት የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ህብረት IGAD መሪዎችና ተወካዮቻቸው በአዲስ አበባ በቪዲዮ መልእክት የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ማእቀብ እንዲጥል ጠይቀዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት አባላት አንዲያስቡበትና ድምጻቸውን እንዲሰጡበት የረፍት ጊዜ ከወሰደ በኋላ በናይጀሪያና ጋቦን አርቃቂነት የቀረበው ስምምነት 2023 በ13 የድጋፍ ድምጽና በቻይናና ራሻ ተአቅቦ ጸድቋል።

በተባበሩት መንግስታት የዩናይትድ ስቴይትስ አምባሳደር ሱዛን ራይስ ይሄ ስምምነት ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ የምትፈጥረውን አለመረጋጋትና ለአሸባሪዎች የምትሰጠውን ድጋፍ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደሚያወግዝ ያሰምርበታል ብለዋል።

“ከዚህ በፊት የነበረውን ስምምነት 1907 ያጠናክራል፥ እናም በኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማእቀቦችን ይጥላል። ከዚያም በተጨማሪ ከማእድን ዘርፍና በውጭ አገር ከሚኖሩ ኤርትራዊያን የሚሰበሰበውን ቀረጥ ላልተፈለገ ለእኩይ ተግባር እንዳታውል ያቅባል” ብለዋር አምባሳደር ራይስ።

ጀርመንም በዚሁ ውሳኔ ላይ የኤርትራ መንግስት የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ህብረት IGAD ለመግባት ያቀረበው ጥያቄ ተፈጻሚ እንዲሆን ጠይቃ፤ ኤርትራ በበኩሏ ከጎረቤቶቿ ጋር እንድትስማማ ገልጻለች።

ውሳኔ 2023 ለኤርትራ ይፋ የፖለቲካ መልእክት የያዘ ነው ያሉት በተ.መ.ድ የጀርመን ቋሚ ልዑክ ፔትር ዊቲግ ኤርትራ “ጎረቤቶቿ መረጋጋት እንዳይኖራቸው የምታደረገውን እንቅስቃሴ ትታ፤ በትብብር መኖር አለባት” ብለዋል።

ቻይናና ራሻ በውሳኔው እጃችን የለበትም ሲሉ በውሃ ታጥበው የተዓቅቦ ድምጽ ሰጥተዋል። የጸጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ፕሬዝደንት የራሻ ፌደሬሽን አምባሳደር ቭ መንግስታቸው በኢጋድ አባሎች የቀረቡት አቤቱታዎች እንደሚያሳስቡት ገልጸው ቪታሊ ቸርኪን በአንዳንድ ለውሳኔ የቀረቡ ጉዳዮች ላይ ግን በቂ ማስረጃ አልነበረም፤ በተለይ ኤርትራ በአዲስ አበባ የአፍሪክ ህብረት ስብሰባ ላይ ፈንጅ ለማፈንዳት አሲራለች የተባለው የተረጋገጠ መረጃ የለውም ብለዋል።

“ምርመራው እንዴት እንደተከናወነ አናውቅም፣ እንዴት እንድተጠናቀቀና በዚህ ጉዳይ ላይ የፍርድ ሂደት ስለመኖሩ የምናውቀው ነገር የለም። ስለዚህ እንዲህ ያለ ከባድ ውንጀላ ለማካተት የተረጋገጠ ማስረጃ ያስፈልግ ነበር። አንድ የሁኔታ አጣሪ ቡድን ይሄን አረጋግጧል ተብሎ ያለበቂ ማስረጃ ማቅረብ ተገቢ አመለካከት አይደልም። በዚያ ላይ የኛ ባለሙያዎች የሁኔታ አጣሪውን ብቃት ሙሉ ድጋፍ አልሰጡትም።”

አምባሳደር ቼርክን አክለውም ምንም እንኳ ራሻ በውሳኔው ገለልተኛ ብትሆንም፤ ለኤርትራ የተሰጠው ጊዜና ውሳኔው የተላለፈበት መንገድ፤ ህጋዊ ነው አሰራሩም ፍትሃዊ ነው ብለዋል።

“ኤርትራ በስልክም ቢሆን አቋሟን እንድታሳውቅ እድሉ ተሰጥቷት ነበር። ይህንን እድል ሊወስዱ በቻሉ ነበር። የአካባቢው መሪዎች በቪዲዮ መልእክታቸውን አሳልፈዋል። ወይንም ደግሞ እዚህ ባሉት ቋሚ መልእክተኛቸው በኩል ተቃውሟቸውን ሊያሰሙ ይችሉ ነበር። እነርሱ ሃሳባቸውን ለመናገር አልፈለጉም፤ ውሳኔው የራሳቸው ነው” ብልዋል ቸርኪን።

የጸጥታው ምክር ቤት ኤርትራ አቋሟን እንድታስረዳ በማሰብ ነበር ለባለፈው ሳምንት ታቅዶ የነበረውን የድምጽ መስጫ ቀነ ቀጠሮ ለሰኞ ያዛወረው።

ኤርትራም አስቀድማ በፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኩል መልእክት ለማሳለፍ ጠይቃ ነበር። የመንግስቱ ቃል አቀባይ አቶ አሊ አብዱ እንደሚሉት የኤርትራ ባለስልጣንት አስመራ በሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ቪዛ ማግኘት አልቻሉም።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሱዛን ራይስ አገራቸው ለልዑካኑ በ24 ሰዓት ውስጥ ቪዛ መስጠቷል ይናገራሉ።

“አርብለት አስመራ በሚገኘው ኢምባሲያችን ለ13 ሰዎች ቪዛ ጠየቁን። አስሩን ቪዛዎች ወዲያውኑ ሰጠናቸው። የተቀሩትን 3 ቪዛዎች በማግስቱ ከአራስት ሰዓት በፊት ሰጠናቸው። ሁሉም ቪዛዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ተሰጥተዋል። የፕሬዝደንት ኢሳያስ ቪዛ ወዲያውኑ በሰዓታት ውስጥ ነው የተሰጠው።”

የኤርትራ መንግስት እነዚህን ሁሉ ከእውነት የራቁ ናቸው ይላል።

XS
SM
MD
LG