በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መናኽሪያዎች ከመሃል አዲስ አበባ በመውጣታቸው ለተጨማሪ ወጪና እንግልት ተዳረግን ሲሉ ተገልጋዮች አማረሩ


መሃል ከተማ የሚገኙ መናኸሪያዎች ወደ አዲስ አበባ መውጫዎች መዛዎራቸው ለከፍተኛ መንገላታትና ወጪ አጋልጦናል በማለት ተገልጋዮች አማረሩ። የከተማዋ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ችግሩ ጊዜያዊ ነው ይላሉ።

ከመሃል ከተማ ታክሲና ሚኒባስ ይዘው ለሚሄዱ ሰዎች ደብረዘይት ናዝሬት አዋሳ የመሳሰሉ ከተሞች ቅርብ ሁንው ቆይተዋል። የለገሃሩ መናኽሪያ ወደ ቃሊቲ ከተዛወረ በኋላ ግን ከተሞቹ ርቀውናል፤ መንገላታቱም በዝቷል፤ ወጪውም ጨምሯል ይላሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ው/ሮ ትብለጥ አስጎዶም መናኽሪያዎች ከመሃል ከተማ እየወጡ ስላሉበት አሰራር ለቪኦኤ ሲናገሩ።

“መናኽሪያዎች ወደ አዋሳኝ መውጫዎች እየወጡ ያሉበት ምክንያት ትራንስፖርት ማስተር ፕላኑን መሰረት በማድረግ ከተማው ውስጥ መጨናነቅ መፈጠር የለበትም። መጨናነቅ ከሚፈጥሩ ምክንያቶች አንዱ መናኽሪያዎች መሃል ከተማ መገኘታቸው ነው።”

እናም የትራንስፖርት ማስተር ፕላኑ በሚያዝዘው መሰረት መናኽሪያዎቹ ወደ አዲስ አበባ መውጫ በሮች እንዲሄዱ እንደሆነም በምሳሌ ያስረዳሉ።

“ለጂማ መግቢያ በር አየር ጤና ላይ የተሰራ መናኽሪያ አለ። አስኮ አካባቢ የተሰራው ደግሞ ወደ ጎጃምና ጎንደር የሚሄዱ ተሳፋሪዎች የሚስተናገዱበት ማለት ነው። የቃሊቲው ደግሞ በምስራቅ በር ላሉ ከተሞች መውጫ ነው። ከፍተኛ መጨናነቅ ይፈጥር የነበረው የለገሃር መናኽሪያ በማስተር ፕላኑ መሰረት ወደ ቃሊቲ ተዛውሯል።በዚህም መጨናነቁን ቀላል በማይባል ሁኔታ ቀንሶታል።”

ከተገልጋዮችና አሽከርካሪዎች የሚደመጠው ግን ለየት ያለ ነው። ከደብረ ዘይት አዲስ አበባ የሚሰራው የሚኒባስ አሽከርካሪ እንዳለው የለገሃሩን መናኽሪያ የማዘዋዎሩ እርምጃ ጥናት የተካሄደበት አይመስልም።

“አንድ ውሳኔ ሲደረግ ከህዝብ ጋር እየተወያዩ ቢሆን አማራጭ ይኖረዋል። ይህን ውሳኔ ከመወሰን በፊት ለህዝቡ በቂ ታክሲ አለዎይ፣ ድሮስ የቃሊቲ ህዝብ ታክሲ ያገኝ ነበረዎይ፣ ከክፍለ ሀገር የሚመጣው ህዝብ በቂ ትራንስፖርት ያገኛል ወይ ተብሎ ምንም ጥናት ሳይካሄድ መናኽሪያው ወደዚህ መጣ እኛም እንድንሰራ ተገደድን፤ የክሱ መጠንም በዛብን ስለዚህ እኛ ወደዚያ አናልፍም።”

ከባለቤታቸውና ልጃቸው ጋር በኮንትራት ታክሲ የመጡ አስተያየት ሰጪም ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

“ቀጥታ ለገሃር ሂደን የምንፈልገውን መኪና ይዘን ወደምንፈልግበት ቦታ እንሄድ ነበረ። አሁን ብዙ መኪና ተገለባብጠህና ብዙ ከፍለህ ነው የምትመጣው። እናም በጣም ፈታኝና አስቸጋሪ ነው።”

በሰላም አውቶብስ ከመቀሌ አዲስ አበባ የገቡት ጥዋት መሆኑን የተናገሩት ሁልት እናቶች፤ ከያዙት እቃ ጋር ወደ ደብረ ዘይት ለመሄድ ያደረጉት ጉዞ አድካሚ ሁኖባቸዋል።

“ችግር ደርሶብናል። እየተጉላላን ነው። መናኽሪያው አማካይ ቦታ ቢሆን ኖሮ ለተሳፋሪውም ለነጋዴውም ጥሩ ነበር። እኛ ለአንድ ቀን እንዲህ የሰለቸን በየቀኑ ለሚመላለስ ምን ያህል አሰልቺ እንደሆነ ነው የምነግርህ።”

በመሆኑም ተገልጋዮቹ ወደ ቃሊቲ ለመሄድም ሆነ ለመመለስ ለእንግልት እንደዳረጋቸው ይናገራሉ። ናዝሬትና አዋሳን ከመሳሰሉ ከተሞች ከምሽቱ 3 ሰዓት የደረሱ ተሳፋሪዎች ወደመሃል ከተማ ለመድረስ ታክሲ አጥተው ሲቸገሩ በቦታው የነበረ የቪኦኤ ዘጋቢ ተመልክቷል። የከተማዋ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ኃላፊ ወ/ሮ ትብለጽ ግን ችግሩ ጊዚያዊ ነው ይላሉ።

“ከመሃል ከተማ ወደ ቃሊቲ የሚሄዱ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ፣ ሃይገር፣ አንበሳ ተሽከርካሪዎችአሉ። ከቃሊቲ መርካቶ የሚሄደው ህዝብ እንደሚስተናገደው ሁሉ ሌላውም ከቃሊቲ ወደ መሀል በሚመጡ ተሽከርካሪዎች ነው የሚስተናገዱት። ስለዚህ ልዩነት ያለው አይመስለኝም። የአቅርቦት ችግሩን እያየን ትራንስፖርት ለማቅረብ ዕቅድ ይዘናል።ችግሮች ለጊዜው ሊከሰቱ ይችላሉ። አሁን በማስተር ፕላኑ መሰረት መስራት ያለብንን መስራት፤ መውጣት ያለበት መውጣት አለበት። ጊዚያዊ ችግር ሳይሆን መታየት ያለበት ዘለቄታው ነው ምክንያቱም አቅርቦትን ከፍላጎት ጋር እናጣጥማለን ብለን ነው እየሰራን ያለነው። ለተወሰነ ጊዜ ችግር ይኖራል ግን እሱንም ለመቅረፍ ሌት ተቀን እየሰራን ነው ያለነው።”

XS
SM
MD
LG