በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መምህራን ከሰኞ ጀምሮ ወደስራ ተመለሱ


“እየተደረገብን ያለው ጫና ጥያቄያችን ሳይመለስ ስራ እንድንጀምር አድርጎናል” መምህራን

በቅርቡ ይፋ የተደረገውን የመምህራን ደመወዝ እርከን ጭማሪ “በቂ አይደለም በማለት” በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚገኙ አንዳንድ ት/ቤቶች፤ የተደረገው የስራ ማቆም እርምጃ አብቅቶ፤ መምህራን ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ወደ ስራ ገበታቸው ተመልሰዋል።

ለቪኦኤ አስተያየታቸውን የሰጡ መምህራን፤ የመማር ማስተማር ሂደቱን ቀጥለው፤ በጎን ጥያቂያቸውን በግልና በህብረት ተደራጅተው እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። እየተደረገብን ያለው ጫና ጥያቂያችን ሳይመለስ ስራ እንድንጀምር አድርጎናል ሲሉ አንዳንድ መምህራን ተናግረዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች፤ በተለይ በአማራ ክልል አንዳንድ ወረዳዎችም አንዳንድ ት/ቤቶች የስራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር። በሰሜን ጎንደር ደምቢያ ዞን የሚገኙ በ6 ት/ቤቶች ለቀናት የዘለቀ የስራ ማቆም አድማ ተካሂዶ ነበር።

በተመሳሳይ መልኩ ስራቸውን እየሰሩ ጥያቄያቸውን ለመንግስት አካላት አቤት ለማለት ወስነው መምህራኑ ወደስራቸው ከተመለሱ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ሆኖም 6 መምህራን ከስራቸው ታግደዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ መምህራን ከሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች የደመወዝ ክፍያ ጋር የተመጣጠነና ወጥ ያልሆነው የደመወዝ እርከን ተገቢ አይደለም በማለት ከትምህርት ምንስቴርና ከሲቪል ሰርቪስ ባለስልጣናት ጋር ውይይትና ድርድር ከጀመሩ ቆይተዋል።

በተለይ በደመወዝ እርከን ማስተካከያ ጥያቂያቸው ላይ እስከ ጥር 30 ምላሽ ለማግኘት ሲጠብቁ የነበረ ቢሆንም፤ በጉዳዩ ላይ በቂ ምላሽ አልተሰጠም ብለው እንደሚያምኑ መምህራኑ ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ መንግስትም በቅርቡ የመምህራንን ህይወት ይለውጣል ያለውን የደመወዝ ጭማሪ እንደየደረጃው ከ69 -140 ብር የደረጃ ማስተካከያ አድርጓል።

ከኑሮ ውድነቱ ጋር የተስተካከለና መሰረታዊ የምግብና የመጠለያ ፍላጎቶችን የሚያሟላ ደመወዝ ይገባናል፤ ጥያቂያችን ተሰሚነት ያግኝ ሲሉ አንዳንድ ት/ቤቶች የስራ ማቆም አድማ ያደረጉ ቢሆንም፤ ከዘገባችን እንደተረዳንው፤ አሁን በመላ አገሪቱ የመማር ማስተማር ሂደቱ ለጊዜው ቀጥሏል፤

በደምቢያ ወረዳ መምህራን ወደ ስራ ገበታቸው ሲመለሱ፤ 6 አስተማሪዎች ከስራቸው ታግደዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናት አቤቱታችንን ይስሙን፤ ድምጻችንን የምናሰማው በሰላማዊ መልኩ ሆኖ ሳለ፤ የወረዳና ቀበሌ ባለስልጣናት የሚያደርሱብንን ወከባ፣ የስራ ማገጃዎችና ክሶች እንቃወማለን ይላሉ ስማቸውን ያልጠቀሱ አንድ መምህር።

ከስራ የታገዱት መምህራን፤ እስካሁን ደመወዛቸው አለመቋረጡን ገልጸው፤ ወደ ስራ ገበታቸው ተመልሰው ጥያቂያቸውን እንደሌሎች የሙያ ባልደረቦቻቸው በማህበራቸው በኩል ጥያቄ ማቅረብ እንደሚፈልጉ ነው የገለጹት።

ሆኖም የወረዳና የቀበሌ ባለስልጣናት ያለምንም አይነት የፍትህ ሂደት፤ የወላጆችና መምህራን ህብረት፤ እንዲሁም በፓርቲ ባለስልጣናት ተሰባስበው ባስቻሉት ችሎት የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርበው፤ መምህራኑን ጥፋተኛ ብለዋቸዋል።

XS
SM
MD
LG