በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ወንጀለኛ የተባሉት ስዊድናዊ ጋዜጠኞች ያለቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ የመብት ተሟጋቾች ጠይቁ


ኮንትነንት ፎቶ ጆርናሊስት ለሚባል የስዊድን የዜና አገልግሎት የሚሰሩት ጋዜጠኞቹ ማርቲን ሸበ እና ዮሃን ፐርሽን በኦጋዴን የተያዙት በአካባቢው ከሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ኦ.ብ.ነግ ታጣቂዎች ጋር በመሆን ከሰሜን ሶማሊያ ሰርገው ከገቡ በኋላ ነው።

የኢትዮጵያ ሰራዊት ጋዜጠኞቹን አጅበው ይንቀሳቀሱ የነበሩ አማጺያን ላይ ገስግሶ ተኩስ በመክፈት፤ ብዙዎቹን ሲገድል ጋዜጠኞቹና ጥቂት ታጣቂዎች ቆስለው ተይዘዋል።

በዚህ አይነት መልኩ ነበር ዓለም-አቀፍ አትኩሮትን የሳበው የጋዜጠኞቹ የፍርድ ሂደት የተጀመረው።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፎቶ ጋዜጠኛውን ዮሃን ፐርሽንና ጸሃፊውን ማርቲን ፐርሽን ሽብርተኝነትን በመደገፍና የሃገር ድንበርን በህገ-ወጥ መልኩ በመሻገር ውንጀል ከአቃቢ ህግ የቀረበውን ክስ ሲመረምር ቆይቷል።

በትናንትናውለት በዚህ እስከ 18ዓመት ሊያሳስር በሚችል ወንጀል ዳኛው ሸምሱ ሰርጋጋ ጋዜጠኞቹን ጥፋተኛ ብለዋል።

ለጋዜጠኞች መብት የሚታገለው Committee to Protect Journalist (CPJ) ውሳኔውን አውግዟል።

“ዮሃን ፐርሽን እና ማርቲን ሸበ እንደጋዜጠኞች ስራቸውን ሲሰሩ ነው የተያዙት። አንድም ቀን ቢሆን በእስር ቤት ማደር አልነበረባቸውም” ብለዋል የሲ.ፒ.ጄ የአፍሪካ መረጃ አጠናቃሪ ሞሀመድ ኪታ።

በጣም የሚያሳዝነት የፍርድ ሂደቱ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነበረው ይላሉ ኪታ።

“በፍርድ ቤት እስኪረጋገጥ ነጻ ናቸው የሚለው መሰረታዊ ህገ-መንግስታዊ መብታቸው ሆን ተብሎ ተጥሷል። ጥፋተኛ መሆናቸው ሲነገራቸው ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ መከላከያ አላቀረባችሁም ነው የተባሉት። መሆን የነበረበት አቃቢ ህግ ላቀረበው ውንጀላ ያለ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ ማስረጃ ማቅረብ ይገባው ነበር”

የመጨረሻ ፍርዱን ያሳለፉት ዳኛ ሸምሱ ሰርጋጋም በመገናኛ ብዙሃን እንደተዘገበው፤ ጋዜጠኞቹ አሸባሪዎችን ላለመደገፋቸውና ለምን በህገ-ወጥ መልኩ ድንበር እንደተሻገሩ ማስረዳትና መከላከል አልቻሉም ብለዋል።

በዓለም ዙሪያ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚሰራው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ጋዜጠኞች በፍጥነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ ጠይቋል።

“ሁለቱ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የጋዜጠኛ ስራ ሊሰሩ እንደሆነ እናምናለን። የታሰሩትም፣ በፍርድ ቤት ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉትም የጋዜጠኝነት ስራቸውን በመስራታቸው ነው” ሲሉ የአምነስቲ የኢትዮጵያና ኤርትራ መረጃ አጠናቃሪ ክሌር ቤስተን አስታውቀዋል።

“የኢትዮጵያ መንግስት ያወጣው አዲስ የጸረ-ሽብር ህግ የፈለጉትን ሰው በጅምላ እንዲወነጅሉ ያስችላቸዋል። ይሄ የሚደረገው የመናገር ነጻነትን ለማፈን ነው”

የኢትዮጵያ መንግስት በኢህአዴግ የ99.6 ከመቶ አብላጫ ድምጽ የሚመራው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈው የጸረ-ሽብር ህግና ተከታትሎ አምስት ድርጅቶችን ሽብርተኛ ብሎ መሰየሙ ይታወሳል። በዚህም መሰረት አልቃይዳ፣ አልሸባብ፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻአውጭ ግንባር፣ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባርና ግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅቶች ተብለዋል።

ከነዚህ ድርጅቶች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት አዲስ በወጣው የኢትዮጵያ የጸረ-ሽብር ህግ መሰረት አሸባሪ ያስብላል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያና ኤርትራ መረጃ አጠናቃሪ ክሌር ቤስተን፤ ጋዜጠኞች የሚያነጋግሩትን ድርጅት ይደግፋሉ ማለት አሳዛኝ አስተሳሰብ ነው ይላሉ።

“አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ ታጣቂ ሃይሎች ጋር መነጋገር፣ ሃሳባቸውን ትደግፋለህ ማለት አይደለም። በፍርድ ቤትም ወንጀለኛ አያስብልም። እኛ እራሳችንም ብንሆን አሸባሪ የተባሉ ሰዎችን እናናግራለን። ሁልጊዜም ቢሆን ለአንድ ሁኔታ ሁለት ድምጾች ይሰማሉ፤ የሁለቱንም ወገን አባባል ለማጣራት መነጋገር ያስፈልጋል” ብለዋል ቤስተን።

በጸረ-ሽብር ህጉ የሚታዩ ክፍተቶችና ህገመንግስታዊ ተቀባይነት ማጣት ብቻ አይደልም በሂደቱ ለጋዜጠኞች በብት የሚከራከረው ሲፒጄ የሚያሳስበው።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋዜጠኞቹን በአደባባይና በሚቆጣጠሯቸው የዜና አውታሮች ወንጀለኛ አድርገው ማቅረባቸው የክሱን ሂደት ተቀባይነት የሌለው ያደርጉታል ይላል ሲ.ፒ.ጄ።

በኢትዮጵያ ቴሌቪዢን የተላለፈ ዘገባ ጋዜጠኞቹ መሳሪያ ይዘው እንደሚያሳይና ምስሉ ሆን ተብሎ በኮምፒውተር የተቀናበረ፤ እንዲሁም ድምጽ የተቀየጠበት በመሆኑ የባለሙያዎችን አስተያየት ሰምቶ ፍርድ ቤቱ መረጃውን ውድቅ ማድረጉን የሲፒጄው የአፍሪካ መረጃ አጠናቃሪ ሞሃመድ ኪታ ያብራራሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ፣ የህዝቡ ንብረት የሆኑ ተቋማትን ከጥቃት ለመከላከልና በአጠቃላይ በአገሪቱ ሰላምን ለማስፈን አሸባሪ ድርጅቶችን ጠብቆ እንደሚዋጋ በተደጋጋሚ አረጋግጧል። ለዚህም ዘመቻ የሚረዳው የጸረ-ሽብር ህግ በፓርላማ ጸድቋል።

ገና ከጅምሩ የጸረ-ሽብር ህጉን፣ የመገናኛ ብዙሃን ህጉንና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የሚያስተዳድሩት ህጎች አንዳንድ አንቀጾች አፋኝና ህገ-መንግስታዊ መስተጋብር የላቸውም በማለት ተቃዋሚዎች፣ የመብት ተሟጋቾችና ምእራባዊያን መንግስታት ተችተዋል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG