በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለመንግስቱ ኃይለማርያም ቤት ሰርታለች የሚሉ ዘገባዎችን ደቡብ ሱዳን አስተባበለች


የደቡብ ሱዳን አስተዳድር ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት መንግስቱ ኃይለማርያም ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ሰርቷል በሚል የተሰራጩ ዘገባዎችን አስተባበለ።

የደቡብ ሱዳን መንግስት ለቪኦኤ በሰጠው ቃል ዘገባዎቹን አስተባብሎ፤ እንዲህ መሰል የሃሰት ወሬዎችን የሚያሰራጩት በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን በኩል ቅራኔ እንዲኖር የሚፈልጉ ሃይሎች ናቸው ብሏል።

ቅዳሜለት የአለማችን 193ኛው አገር ሆና ነጻነቷን ያወጀችው ደቡብ ሱዳን፤ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት መንግስቱ ኃይለማርያም ዘመናዊ የመኖሪያ ሰርታ አጠናቃለች በሚል የተሰራጩ ዘገባዎች የሃሰት ወሬዎች ናቸው ሲሉ የመንግስቱ ቃል አቀባይ በተለይ ለቪኦኤ ገልጸዋል።

መንግስቱ ኃይለማርያም በስልጣን ላይ በቆዩበት ወቅት ለደቡብ ሱዳን አማጽያን ያደርጉት የነበረውን እርዳታ ታሳቢ በማድረግና፣ የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጭ ጦር SPLA መሪ የነበሩት ዶር ጆን ጋራንግንና በርካታ ስደተኞችን በኢትዮጵያ እንዲኖሩ በመፍቀዳቸው፤ ውለታ ለመመለስ ደቡብ ሱዳን ለመንግስቱ ቤተሰቦች ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት መገንባቷን ዘገባዎች አትተዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግስት ቃል አቀባይ ዶር በርናባ ቤንጃሚን፤ ዘገባዎቹ ከእውነት የራቁ ናቸው ሲሉ አስተባብለዋል።

“ይሄ በእውነቱ የደከመ ውሸት ነው። አፋቸውን በውሸት ያጨቁ አፍሰህ አቅመኞች የሚያስወሩት ነው። ማንም ሰው እንደሚያውቀው የቀድሞው ፕሬዝደንት መንግስቱ ኃይለማርያም ጥገኝነት አግኝተው የሚኖሩት በዝምባብዌ ነው። ደቡብ ሱዳን መጥተው አያውቁም፤ እኛም ለሳቸው ጎጆቤት እንኳን አልሰራንላቸውም።”

የመንግስቱ አስተዳድር የደቡብ ሱዳን አማጺያን SPLA ሃይሎችን ለረጂም አመታት አግዟል። ለስደተኞች መጠለያ ከመስጠት ጀምሮ ወታደራዊ ምክርና እርዳታ እስከመስጠት ይደርስ ነበር ትብብራቸው። ይህንን ጊዜ በማስታወስ ለመንግስቱ ቤተሰብ በዝምባብዌም ሆነ በደቡብ ሱዳን ቤት አልሰራንም የሚሉት ዶር. ባርናባ፤ ይህንን ወሬ የሚያስወሩት በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማደፍረስ የሚሹ ሃይሎች ናቸው ብለዋል።

“በአቢዮ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ተሳትፎ የሚያውቁና የማይወዱ ሃሎች የሚያወሩት ወሬ ነው። በአቢዮ ኢትዮጵያ የሚኖራትን ሚና ከጥርጣሬ ውስጥ ለማስገባት የታለመ ነው። አላማቸው ምንድን ነው? ተመልከቱ የደቡብ ሱዳን መንግስት ኢትዮጵያ የማትወደውን እያደረገ ነው፤ እናም እናጣላችሁ ነው” ብለዋል ዶር. ባርናባ

“ስለዚህ ይሄ ውሸት ነው። ኢትዮጵያ ብንሆን ውሸት ተቀብሎ በማተሙ ይሄንን ጋዜጣ እንከሰዋለን። የደቡብ ሱዳን መንግስት ያላደረገውን ነው አደረገ የሚሉት፤ ውሸት ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በአቢዮ ላይ ለሚሰፍር የሰላም አስከባሪ ሃይል ከ4500 በላይ ወታደሮች ለማስፈር እንደፈቀደችና እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል።

በነዳጅ ሃብቷ የምትታወቀው የአቢዮ ግዛት ሰሜንም ደቡብም ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ ያነሳሉ።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG